ሞስኮ የዩክሬንን አንድ አምስተኛ ግዛት አሁንም እንደያዘች ነው
ዩክሬን በደቡብ ምስራቅ ግንባር ድል እየቀናት እንደሆነ ገለጸች።
የዩክሬን ጦር በደቡብ ምስራቅ ግንባር በሩሲያ ጦር ላይ ባደረገው የመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ስኬት እንዳገኘ ገልጿል።
ይህ የተባለው ጦሩ የሩሲያ ጠንካራ ምሽግ ሆኖ ያገለገለውን አካባቢ ነጻ መውጣቱን ካወጀ አንድ ቀን በኋላ ነው።
የዩክሬን ጦር በዶኔትስክ ክልል ዩሮዚን በተባለ መንደር ተጨማሪ ድሎችን እያገኘ መሆኑን አስታውቋል።
ዩሮዚን ኪየቭ ከሀምሌ መጨረሻ በኋላ መልሶ መያዟን ያስታወቀች የመጀመሪያዋ መንደር ናት።
ይህም ኪየቭ ካለ አየር ድጋፍ በከፍተኛ ፈንጂ የታጠረውን የሩሲያ የመከላከያ መስመሮች ለመስበር ያጋጠማትን ፈተና የሚያመለክት ነው ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
በተጨማሪም በሰሜን ምስራቅ ካርኪቭ ክልል እና ከባክሙት በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኝ ምስራቃዊ መንደር አካባቢ ከባድ ውጊያ መደረጉ ተነግሯል።
ባክሙት በግንቦት ወር ደም አፋሳሽ ጦርነት ከተደረገ በኋላ በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ውስጥ ያለች ከተማ ናት።
ሩሲያ ክራይሚያን ጨምሮ አብዛኛው የሉሃንስክ እና የዶኔትስክ ክልል፣ ዛፖሪዝሂያ እና ኬርሰን አካባቢዎችን ጨምሮ የዩክሬንን አንድ አምስተኛ የሚጠጋ ግዛት ትቆጣጠራለች።
ኪየቭ በሰፋፊ የሩሲያ ፈንጂዎች እና በጠንካራ የሩሲያ መከላከያ መስመሮች የተነሳ የመልሶ ማጥቃት እርምጃዋ ከሚፈልገው በላይ እንደዘገየ ተነግሯል።