የአሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ስምምነት የኮሪያ ልሳነ ምድርን ቀውስ ያባብሳል - ሩሲያ
ሀገራቱ ባለፈው ሳምንት የተፈራረሙት የኒዩክሌር ስምምነት የጦር መሳሪያ እሽቅድምድም ያመጣል በሚል ነው ሞስኮ ተቃውሞዋን ያሰማችው
አሜርካ ከ40 አመታት በኋላ የኒዩክሌር ተሸካሚ መርከቦች ወደ ደቡብ ኮሪያ እንደምትልክ አስታውቃለች
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ባለፈው ሳምንት የተፈራረሙት ስምምነት የኮሪያ ልሳነ ምድርን ወደባሰ ቀውስ ውስጥ እንደሚያሰገባው ሩሲያ ገልጻለች።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል በዋይትሃውስ ከአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን ጋር መምከራቸው ይታወሳል።
በዚህም ዋሽንግተን ኒዩክሌር ተሸካሚ መርከቦቿን ወደ ሴኡል ለመላክ ቃል መግባቷ አይዘነጋም።
አሜሪካ በኒዩክሌር እቅዶቿ ዙሪያም የደቡብ ኮሪያን ባለሙያዎች ለማሳተፍ የሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ይህ የኒዩክሌር ስምምነት የኮሪያ ልሳነ ምድርን ብቻ ሳይሆን የአለም ደህንነትን ያናጋል የሚል መግለጫን አውጥቷል።
የአሜሪካ እና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በእስያ ሀገራት መስፋፋትን የተቃወመችው ሞስኮ፥ ስምምነቱ የጦር መሳሪያ እሽቅድምድም ያመጣል ብላለች።
አሜሪካ በበኩሏ ሞስኮ ለፒዮንግያንግ ከምታሳየው ድጋፍ ባሻገር የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ የኒዩክሌር የጦር መሳሪያዎቿን ለመጠቀም በተደጋጋሚ መዛቷን በመጥቀስ ወቀሳውን ታስተባብላለች።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው የዋሽንግተን እና ሴኡል ስምምነት ፍጥጫውን ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖረው ነው የገለጸው።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እህት ኪም ዮ ጆንግም የሞስኮን ሀሳብ የሚያጠናክር መግለጫ መስጠታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ፒዮንግያንግ በደህንነቴ ላይ ተጋርጧል ላለችው የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ አጋርነትና የኒዩክሌር ስምምነት ምላሽ እንደምትሰጥም ዝተዋል።
ሰሜን ኮሪያ ከ2022 ወዲህ ከ100 በላይ የሚሳኤል ሙከራዎችን ያደረገች ሲሆን፥ የኒዩክሌር መርሃ ግብሯን አጠናክራ መቀጠሏ ለአሜሪካ እና አጋሮቿ ከባድ ስጋት ደቅኗል።