ጃፓን የሰሜን ኮሪያ ሳተላይትን ለመምታት ተዘጋጅቻለሁ አለች
ሰሜን ኮሪያ በታህሳስ ወር "የስለላ ሳተላይት" ለማምጠቅ "የመጨረሻ ምዕራፍ" ሙከራ ማድረጓን አስታውቃለች
ፒዮንግያንግ ከአሜሪካና ከደቡብ ኮሪያ የሚደርሰውን ስጋት ለመከላከል "ሰላይ ሳተላይት" ለማምጠቅ መወሰኗን ገልጻለች
ጃፓን የሰሜን ኮሪያ ሳተላይት ወደ ግዛቴ ድርሽ ቢል አስቀድሜ ለመምታት ተዘጋጅቻለሁ ብላለች።
የጃፓን መከላከያ ሚንስትር ያሱካዙ ሃማዳ የሀገሪቱ ጦር የፒዮንግያንግ የስለላ ሳተላይት በጃፓን ግዛት ውስጥ ቢገባ ለመምታት እንዲዘጋጅ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ሃማዳ የራስ-መከላከያ ሰራዊት አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርግ ያዘዙ ሲሆን፤ የባላስቲክ ሚሳይሎችን ለመምታትም ማዘዝ እንደሚችሉ መከላከያ ሚንስቴር በመግለጫው ገልጿል።
ትዕዛዙ “የባላስቲክ ሚሳይል ቢወድቅ ጉዳቱን ለመቀነስ” ወታደሮቹን ወደ ኦኪናዋ ደቡባዊ ግዛት ለማሰማራት ዝግጅት ማድረግን ያካትታል መባሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነችውን የስለላ ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ እርምጃው ከአሜሪካ እና ከደቡብ ኮሪያ የሚደርሰውን ስጋት ለመከላከል እንደሆነ የፒዮንግያንግ የመንግስት መገናኛ ብዙኸን ዘግበዋል።
ሰሜን ኮሪያ በታህሳስ ወር ለ"ሰላዩ ሳተላይት" "የመጨረሻ ምዕራፍ" ያለችውን ሙከራ ማድረጓን አስታውቃለች።
ሀገሪቱ እስከ ሚያዚያ ድረስ ወደ ህዋ ለማምጠቅ ዝግጅቷን እንደምታጠናቅቅም ተናግራለች።በደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ ሴኡል በሙከራው ወቅት በሰላዩ ሳተላይት የተነሱ ምስሎች መለቀቃቸው ይታወሳል።