ሩሲያ በዩክሬን ድንበር የታክቲካል ኒዩክሌር መሳሪያ ልምምድ ጀመረች
ልምምዱ ምዕራባውያን በዩክሬኑ ጦርነት ይበልጥ ጣልቃ እንዳይገቡ ለማስጠንቀቅ ያለመ ነው ተብሏል
ሞስኮ ከ1 ሺህ 500 በላይ ታክቲካል የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎች እንዳላት ይገመታል
ሩሲያ ታክቲካል የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎችን እንዴት መተኮስ እንደሚቻል በዩክሬን ድንበር ልምምድ እያካሄደች ነው።
በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትዕዛዝ እየተካሄደ ያለው ልምምድ ምዕራባውያን ሀገራት በዩክሬኑ ጦርነት የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዲያስቡበት ለማስጠንቀቅ ያለመ ነው ተብሏል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከወር በፊት የአውሮፓ ወታደሮች ወደ ዩክሬን በመግባት ሩሲያን ሊፋለሙ ይችላሉ ማለታቸው ሞስኮን ማስቆጣቱ ይታወሳል።
የብሪታንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንም ኬቭ ከለንደን በተላኩላት የጦር መሳሪያዎች በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጭምር ጥቃት ማድረስ ትችላለች የሚል አስተያየት መስጠታቸው አይዘነጋም።
የሞስኮ ታክቲካል የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎች ልምምድም ምዕራባውያኑን ለማስጠንቀቅ ብሎም በዩክሬኑ ጦርነት ፈጣን ድልን ለማስመዝገብ እንደሚያስችል ታምኖበታል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የመጀመሪያው ምዕራፍ ልምምድ “እስክንድር” እና “ኪንዛሃል” የተሰኙት ሚሳኤሎችን ያካተተ ነው።
ታክቲካል የኒዩክሌር መሳሪያዎች ከተሞችን ከሚያጠፉት ስትራቴጂክ የኒዩክሌር መሳሪያዎች አንጻር የጥፋት አቅማቸው ዝቅተኛ ነው።
ሩሲያ 1 ሺህ 558 ታክቲካል የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ አረር እንዳላት የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ፌደሬሽን መረጃ ቢያሳይም አሃዙ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ይገመታል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ወታደሮች የኒዩክሌር አረሮቹን በኪንዝሃል ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ማስወንጨፊያ ሲያስገቡና ሚሳኤሎቹ በተሽከርካሪዎች ተጭነው ወደሚተኮሱበት ስፍራ ሲንቀሳቅሱ የሚያሳይ ቪዲዮ ለቋል።
ቤላሩስም ትሳተፍበታለች የተባለው ልምምድ ተኩስ ስለማካተቱ ግን አልተጠቀሰም።
ልምምዱን በትኩረት እየተመለከቱት የሚገኙት ምዕራባውያን ሀገራት ሞስኮ እነዚህን የኒዩክሌር መሳሪያዎች ወደ ጦር ግንባር የምትልክ ከሆነ ምን አይነት እርምጃ እንውሰድ በሚለው ዙሪያም ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ይጠበቃል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።