ምዕራባውያን ሩሲያ የኒዩክሌር ጦርነት እንድትጀምር እየገፋፏት ነው - ፑቲን
ፕሬዝዳንቱ ምዕራባውያን ወደ ዩክሬን ወታደሮችን ከላኩ ከአዶልፍ ሂትለርም ሆነ ናፖሊይን ቦናፓርቴ የከፋ እጣ ፈንታ ይገጥማቸዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል
የፑቲን ማስጠንቀቂያ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ከሰሞኑ ለሰጡት አስተያየት ምላሽ ነው ተብሏል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን ሀገራት የኒዩክሌር ጦርነት እንዲጀመር እየገፋፉን ነው ሲሉ ወቀሱ።
ምዕራባውያን ወደ ዩክሬን ወታደሮችን በማዘመት ሩሲያን የሚዋጉ ከሆነ ሞስኮ ሀገራቱ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንደምትፈጽምም ዝተዋል።
ከአምስት ቀናት በፊት ሁለት አመት የደፈነው የዩክሬን ጦርነት ሩሲያ ከ1962ቱ የኩባ የሚሳኤል ቀውስ በኋላ ከምዕራባውያን ጋር ከባድ ውጥረት ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መስፋፋትን ደጋግመው የተቃወሙት ፑቲን ሞስኮ ከኔቶ ጋር በቀጥታ ጦርነት ውስጥ ከገባች አደገኛ ሁኔታ እንደሚፈጠር ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
የ71 አመቱ ፕሬዝዳንት ዛሬ ለሀገሪቱ ህግ አውጪዎች እና ምሁራን ባደረጉት ንግግርም ምዕራባውያን ሩሲያን ለማዳከም የሚያደርጉት ሙከራ ከባድ ችግር ይፈጥራል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የምዕራባውያን ሀገራት መሪዎች “በሩሲያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት” ምን ያህል አደገኛ መሆኑን በሚገባ የተረዱት አይመስልም ሲሉ መደመጣቸውንም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
የፑቲን ማስጠንቀቂያ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ወደ ዩክሬን ወታደሮችን በመላክ ዙሪያ ለሰጡት አስተያየት ምላሽ እንደሚሆን ቢጠበቅም በስም አልጠቀሷቸውም።
ማክሮን የኔቶ አባል የሆኑ የአውሮፓ ሀገራት ወደ ዩክሬን ወታደሮችን በመላክ ዙሪያ ስምምነት ላይ ባይደርሱም “የሩሲያ መሸነፍ የመላው አውሮፓ ድል በመሆኑ” እንደ መጨረሻ አማራጭ ሊታይ ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጂ አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ጀርመን እና ሌሎች የአውሮፓ ህብረትና የኔቶ አባል ሀገራት የማክሮንን አስተያየት የሚያስተባብሉ መግለጫዎችን ማውጣታቸው አይዘነጋም።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዛሬው ንግግራቸው “ምዕራባውያን በግዛታቸው ውስጥ ዘልቀው ገብተው ጥቃት የሚፈጽሙ የጦር መሳሪያዎች እንዳሉን በሚገባ መገንዘብ አለባቸው” ማለታቸው ተዘግቧል።
ከመጋቢት 15 – 17 በሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለአምስተኛ የስልጣን ዘመን የሚፎካከሩት ፑቲን ሀገራቸው በአለማችን ቀዳሚ ያደረጋትን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ እያዘመነች መሆኑንም ተናግረዋል።
የሀገሪቱ “ስትራቴጂክ ሃይፐርሶኒክ ኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎች” ለየትኛውም ጥቃት ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
ፑቲን ምዕራባውያን ፖለቲከኞች የናዚ ጀርመኑ አዶልፍ ሂትለርም ሆነ የፈረንሳዩ ናፖሊዮን ቦናፓርቴ ሩሲያን ለመውረር ሲሞክሩ ከገጠማቸው ይማሩ ዘንድም ቆጣ ብለው መክረዋቸዋል።
“(ምዕራባውያን) ጦርነት የካርቱን ፊልም ይመስላቸዋል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ፥ ጸብ ማጫሩን ካላቆሙ ከሂትለርም ሆነ ናፖሊዮን የከፋ እጣ ፈንታ ይገጥማቸዋል ማለታቸውንም ታስ አስነብቧል።