200 ታክቲካል ኒዩክሌር መሳሪያ እንዳላት የሚነገርላት አሜሪካ አለማችን ከ1962ቱ የኩባ የሚሳኤል ቀውስ በኋላ ትልቁ የኒዩክሌር አደጋ አንዣቦባታል ብላለች
ሩሲያ ታክቲካል የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን በቤላሮስ ለማስፈር ከስምምነት ላይ መደረሱን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናግረዋል።
ስምምነቱ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ፉክክርን ለመግታት የተደረሰውን ስምምነት የሚጋፋ አለመሆኑንም ፕሬዝዳንት ፑቲን ገልጸዋል።
የአለማችን ቀዳሚዋ ኒዩክሌር የታጠቀችው ሀገር አሜሪካ ግን ምድራችን ከ1962ቱ የኩባ የሚሳኤል ቀውስ በኋላ ትልቁ የኒዩክሌር አደጋ አንዣቦባታል ስትል አስጠንቅቃለች።
ሞስኮ ግን ምዕራባውያን ጉዳዩን ያልተገባ ትርጉም ሰጥተው አጋነውታል እያለች ነው።
ታክቲካል የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ምንድን ነው?
የጦር መሳሪያዎች ላይ ምርምር የሚያደርጉ ምሁራን እና የጦር መሳሪያ ተቆጣጣሪዎች በታክቲካል የኒዩክሌር የጦር መሳሪያዎች ዙሪያ አንድ አይነት ብያኔ ለመስጠት ለአመታት ተከራክረዋል።
በአንድ ነገር ግን ይስማማሉ፤ ታክቲካል የኒዩክሌር መሳሪያዎች በአውደ ውጊያዎች ላይ የተወሰነ ድልን ለመቀዳጀት የሚውሉ እንጂ ትልልቅ ከተሞችን በአንዴ ዶግ አመድ የሚያደርጉ አለመሆናቸውን።
ሩሲያ ምን ያህል ታክቲካል የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ እንዳላት በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም ይላል የሬውተርስ ዘገባ።
አሜሪካ ግን ሩሲያ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ታክቲካል የኒዩክሌር አረሮች እንዳሏት ታምናለች፤ ይህም ከዋሽንግተን በ10 እጥፍ ብልጫ እንዳለውም ትገልጻለች።
የኒዩክሌር አረሮቹ በሚሳኤሎች፣ በባህር ውስጥ በሚምዘገዘጉ ቶርፒዶዎች፣ ከአየር ወይም ከየብስ ላይ በሚተኮሱ ቢ 16 ኒዩክሌር ቦንቦች (ግራቪቲ ቦምብ) ላይ ተገጥመው ሊተኮሱ ይችላሉ። ወደተፈለገው ስፍራ በመውሰድም ባሉበት (ሳይወነጨፉ) ሊተኮሱ እንደሚችሉ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
አሜሪካ 200 የሚጠጉ ታክቲካል ኒዩክሌር መሳሪያዎች እንዳሏት የሚገልጸው የሬውተርስ ዘገባ፥ ከዚህ ውስጥ ግማሹ በአውሮፓ ሀገራት ይገኛሉ ይላል።
የአሚሪካ 30 ሴንቲሜትር የሚረዝሙ ቢ 61 ኒዩክሌር ቦምቦች ከ0 ነጥብ 3 እስከ 170 ኪሎቶን የሚመዝኑ ሲሆን፥ በጣሊያን፣ ጀርመን፣ ቱርክ፣ ቤልጂየም እና ኔዘርላንድስ በሚገኙ የአየር ጣቢያዎቿ ይገኛሉ።
አሜሪካ በፈረንጆቹ 1945 በጃፓኗ ሄሮሺማ የጣለችው አቶሚክ ቦምብ 15 ኪሎቶን የሚመዝን ነው።
ሩሲያ ወደ ቤላሩስ እልካቸዋለሁ ያለቻቸው ታክቲካል ኒዩክሌር መሳሪያዎች ከአቶሚክ ቦምብ አንጻር የከፋ ጉዳት የሚያደርሱ አይደሉም ቢባልም ዋሽንግተንም ሆነች ኬቭ ከፍተኛ ስጋት አላቸው።
የኒዩክሌር ስምምነቱ ተጥሷል?
ሶቪየት ህብረት በፈረንጆቹ 1991 ከመፈረካከሷ በፊት 22 ሺህ ገደማ ታክቲካል ኒዩክሌር መሳሪያዎች እንዳሏት ይነገራል።
አሜሪካ ደግሞ 11 ሺህ 500 ኒዩክሌር አረር የተሸከሙ ታክቲካል ኒዩክሌር መሳሪያዎች ነበሯት። ይሁን እኝጂ አብዛኞቹ ታክቲካል ኒዩክሌር መሳሪያዎች በሀገራቱ እንዲወድሙ ተደርጓል።
ሩሲያ አሁን ላይ የቀሯት ታክቲካል ኒዩክሌር መሳሪያዎ በ30 ወታደራዊ ማዘዣዎች የሚገኙ ሲሆን በፕሬዝዳንት ፑቲን ቀጥታ ትዕዛዝ ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ ይነገራል።
ከሶቪየት መፈረካከስ በኋላ በቤላሩስ፣ ዩክሬን እና ካዛኪስታን የነበሩ የሶቪየት ሰራሽ ኒዩክሌር መሳሪያዎችን ወደ ሞስኮ ለመመለስ ሰፊ ጥረት ያደረገችው ዋሽንግተንም የትናንቱን የፑቲን ውሳኔ አደገኛ ነው እያለች ነው።
ውሳኔው የኒዩክሌር መሳሪያዎችን ኒዩክሌር ወዳልታጠቁ ሀገራት መውሰድን የሚከለክለውን ስምምነት የሚጥስ ስለመሆኑም ገልጻለች።
ሞስኮ ግን ታክቲካል ኒዩክሌር መሳሪያዎች እንደ አቶሚክ ቦምብ አውዳሚ አለመሆናቸውን በማንሳት ስምምነቱን አልጣስኩም ማለቷን ገፍታበታለች።