ሩሲያ 'አብርሃም' የተባለውን የአሜሪካ ታንክ ለማረከ ወታደር ሽልማት አዘጋጀች
አንድ ታንክ ለማረከ ወይም ላወደመ ወታደር 72 ሺህ ዶላር እንደምትሸልምም ገልጻለች
ምዕራባዊያን ለዩክሬን መጠነ ሰፊ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን በመለገስ ላይ ናቸው
ሩሲያ የአሜሪካውን 'አብርሃም' የተሰኘውን ታንክን ለማረከ ወታደር ሽልማት አዘጋጀች፡፡
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ የቀሩት ሲሆን ጦርነቱ በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን እያስተናገደ ቀጥሏል፡፡
በአጭር ወራት ውስጥ በድርድር ይቋጫል ተብሎ ተጠብቆ የነበረው ይህ ጦርነት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን የአሜሪካ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን በየጊዜው አዳዲስ የጦር መሳሪያ ድጋፎችን እያደረጉ ናቸው፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ በዓለማችን የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ እጅግ ዘመናዊ የሚባሉት የጀርመኑ ሊዮፓርድ እና የአሜሪካው አብርሃም ታንኮች ለዩክሬን ለመስጠት ዝግጅቱ ተጀምሯል፡፡
እነዚህን ዘመናዊ የጦር ሜዳ ታንኮች ለዩክሬን ለመስጠትም ሀገራቱ ይህን ታንክ ማንቀሳቀስ የሚችሉ ዩክሬናዊያንን የማሰልጠኑ ስራ በመካሄድ ላይ እንደሆነም ተሰምቷል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ ምዕራባዊያን ለዩክሬን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማድረጋቸው ወደ ዓለም ጦርነት ይወስደናል ስትል በማስጠንቀቅ ላይ ናት፡፡
ምዕራባዊያን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እንሰጣለን ማለታቸውን ተከትሎም ሩሲያ በተለይ የአሜሪካ ስሪት የሖነው አብርሃም ታንክን ላወደመ ወይም ለማረከ ወታደር ሽልማት ማዘጋጀቷን አስታውቃለች፡፡
አንድ ታንክ ለማረከ ወታደርም አምስት ሚሊዮን ሩብል ወይም 72 ሺህ ዶላር እንደምትሸልም መግለጿን ሮይትርስ ዘግቧል፡፡
የሩሲያው ፎረስ የሀይል ልማት ኩባንያ እንዳለው የሩሲያ ወታደሮች ከስድስት ወር በኋላ ወደ ዩክሬን ምድር ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው አሜሪካ እና ጀርመን ሰራሽ አብርሃም እና ሊዮፓርድ ታንኮችን ለሚማርኩ አልያም ለሚያወድሙ ወታደሮች ልዩ ሽልማት አዘጋጅቼያለሁ ብሏል፡፡
እንዲሁም በነዚህ ታንኮች ላይ ማንኛውንም አይነት ጥቃት ላደረሱ የሩሲያ ወታደሮች ደግሞ 7 ሺህ 200 ዶላር እከፍላለሁም ብሏል፡፡
ሩሲያ ከሰሞኑ ምዕራባዊያን ለዩክሬን ማንኛውንም አይነት የጦር መሳሪያዎች ቢለግሱ ለውጥ አያመጡም ሁሉንም “አቃጥላቸዋለሁ” ማለቷ ይታወሳል፡፡