አሜሪካ ለደቡብ ኮሪያና ፖላንድ ታንክና ሄሊኮፕተሮችን ለመሸጥ ተስማማች
በዚህ አመት 250 ታንኮችን ለፖላንድ የሸጠችው ዋሽንግተን፥ ተጨማሪ 116 ታንኮችን ወደ ዋርሳው እንድትልክ ኮንግረንሱ አፅድቆታል
ሴኡልም ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ሄሌኮፕተሮች ከአሜሪካ ሊሸጥላት ነው
አሜሪካ ከ5 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ለደቡብ ኮሪያና ፓላንድ ልትሸጥ ነው።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የመሳሪያ ሽያጩን ጉዳይ የአሜሪካ ኮንግረንስ አፅድቆታል።
አሜሪካ ለፓላንድ 3 ነጥብ 75 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ 116 ታንኮችን ነው ለመሸጥ የተስማማችው።
ዋርሳው በዚህ አመት ሚያዚያ ወር 250 አብራምስ የተሰኙ ታንኮችን ከዋሽንግተን መግዛቷ ይታወሳል።
አሜሪካ በአዲሱ ስምምነት ተጨማሪ 116 ታንኮችን ለፖላንድ መሸጧ አሁናዊና ቀጣይ የደህንነት ስጋቶቿን ለመመከት ያስችላታል ተብሏል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት የዩክሬኑን ጦርነት የኔቶ አባል በሆነችው ፖላንድ በኩል ለመመከትም ይሄው ስምምነት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተነስቷል።
ከታንኮቹ ባሻገር ዘመናዊ የጦር ተሽከርካሪዎችና ታንኮችን በባህር የሚያሳልፉ ድልድዮች ዋርሳው ከዋሽንግተን ታገኛለች።
አሜሪካ ለደቡብ ኮሪያም 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ 18 ሄሊኮፕተሮችን ለመሸጥ ተስማምታለች።
ሄሊኮፕተሮቹ ለድንገተኛ አደጋ እና አፋጣኝ ድጋፍ ለማድረስ ይውላሉ ተብሏል።
ይሁን እንጂ ሴኡል ከፒዬንግያንግ ሊቃጣባት የሚችል ጥቃትን እንድትመክት ዋሽንግተን የትኛውንም ድጋፍ እንደምታደርግ ማረጋገጧ ይታወሳል።