ሞስኮ ውሳኔውን “እጅግ አደገኛ” በማለት አውግዛዋለች
አሜሪካና ጀርመን ለዩክሬንን በደርዘን የሚቆጠሩ የጦር ታንኮች ለማስታጠቅ ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።
ሞስኮ ውሳኔውን “እጅግ አደገኛ” በማለት አውግዛዋለች።
በጀርመን የሩሲያ አምባሳደር ሰርጌይ ኔቻዬቭ “ይህ እጅግ አደገኛ ውሳኔ ጦርነቱን ወደ አዲስ የግጭት ደረጃ ያሸጋግራል” ብለዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ የተገባላቸውን ቃል አድንቀው አጋሮች ብዙ ታንኮችን በፍጥነት እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።
"አሁን ቁልፉ ፍጥነት እና ብዛት ላይ ነው። ኃይላችንን በፍጥነት ማሰልጠን፤ ታንኮችን ደግሞ በፍጥነት ወደ ዩክሬን ማቅረብ ነው" ብለዋል።
ዩክሬን የሩሲያን የመከላከያ መስመሮችን በመስበር በደቡብ እና በምስራቅ "በወረራ የተያዙባትን" ግዛቶች ለማስመለስ ለጦር ኃይሏ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዘመናዊ ታንኮችን ስትፈልግ ቆይታለች።
ዩክሬን እና ሩሲያ በዋናነት በሶቪየት ዘመን የተመረቱ ቲ-72 የተባሉ ታንኮችን እንደሚጠቀሙ ሮይተርስ ዘግቧል።
ጀርመን 14 ታንኮችን ለመስጠት ትናንት ውሳኔ ማሳለፏ የሚታወስ ነው።
በርሊን "ሊዮፓርድ ሁለት" የተባሉትን በመላው አውሮፓ የኔቶ ኃይል የታጠቃቸውን ታንኮችን አቀርባለሁ ካለች ከሰዓታት በኋላ፤ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን "31 ኤም አንድ አብራምስ" የተባሉ ታንኮችን ለማቅረብ ወስነዋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭም ሀገራቸው የአሜሪካን ኤም1 አብራምስ ታንኮች ለማደባየት መዘጋጀቷን ተናግረዋል።
የአሜሪካ እና ጀርመን ታንኮች በጦርነቱ የሚለውጡት አንዳች ነገር እንደሌለም ነው ፔስኮቭ የተናገሩት። ሞስኮ የምዕራባውያኑ ድጋፍ 11ኛ ወሩን የያዘው ጦርነት አለምን ወደ ኒዩክሌር ጦርነት እንዳያስገባት እያለች ማስጠንቀቋን ቀጥላለች።