ጀርመን ሰራሹ ታንክ በዩክሬን ጦርነት እጅግ ተፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
በርሊን ሊዮፓርድ 2 የተሰኘውን ታንኳን ወደ ኬቭ እንድትልክ ከምዕራባውያን ጫናው በዝቶባታል
ሞስኮ በበኩሏ ብዙ የተወራለት ሊዮፓርድ 2 “በጦርነቱ ምንም ለውጥ አያመጣም አደባየዋለሁ” እያለች ነው
ጀርመን 11ኛ ወሩን በያዘው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ተሳትፎዋ እንዲያድግ ጫናው በርትቶባታል።
መራሂ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ ሊዮፓርድ 2 የተሰኘውን ታንክ ወደ ዩክሬን እንዲልኩ ከምዕራባውያን ለሚነሳው ጥያቄም እስካሁን አዎንታዊ ምላሽ አልስጡም።
አውሮፓዊቷ ሀገር ታንኮቿን ወደ ዩክሬን መለኳ በጦርነቱ ቀጥታ እንደመሳተፍ ትቆጥረዋለች።
አሜሪካ አብራምስ 1 ታንኳን እስካለከች ድረስ በርሊን ታዋቂውን ሊዮፓርድ 2 ታንክ ወደ ኬቭ አልክም በሚለው አቋሟም እንደጸናች ነው።
ሶቪየት ሰራሽ ቲ 72 ታንኮችን የምትጠቀመው ዩክሬን እስካሁን ከብሪታንያ ብቻ ነው ቻሌንጀር 2 የተሰኘውን ታንክ ያገኘችው።
አሜሪካም ሆነች ሌሎች የኬቭ አጋሮች ሞስኮ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎቻችን ትሰርቃለች በሚል ታንኮችን ከመላክ ተቆጥበዋል።
ሊዮፓርድ 2 ታንኮችን የሚጠቀሙ የአውሮፓ ሀገራት ወደ ኬቭ ታንኩን ለመላክ የበርሊንን ፈቃድ ለማግኘት መገደዳቸውም የሊዮፓርድ 2 ታንክ መነጋገሪያ ርዕስነትን አጉልቶታል።
ዩክሬን ሊዮፓርድ 2 ታንኮችን ለምን አጥብቃ ፈለገች?
ጀርመን ሰራሹ ሊዮፓርድ 2 ታንክ በምዕራቡ አለም ሁነኛ የጦር መሳሪያ ተደርጎ ይወሰዳል።
የጀርመን መከላከያ ሃይል ተቋም ካውስ ማፋይ ዋግማን ከፈረንጆቹ 1978 ጀምሮ ከ3 ሺህ 500 በላይ ሊዮፓርድ 2 ታንኮችን አምርቷል።
ከ60 ቶን በላይ የሚመዝነውና በናፍጣ የሚሰራው ታንክ እስከ 5 ኪሎሜትር ትክክለኛ ኢላማውን መምታት ይችላል። ፖላንድ፣ ኖርዌይ፣ ስፔን፣ ስዊድን እና ቱርክን ጨምሮ 20 ሀገራት ይህን ታንክ ይጠቀሙበታል።
ይህም ሊዮፓርድ 2 ኬቭ ከገባ ጎረቤቶቿ ፈጣን ጥገና እና የባለሙያ ስልጠና እንዲሰጡ እድል ይሰጣል።
በርሊን በአሁኑ ወቅት 350 ታንኮች አሏት፤ ይህም በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ከነበሯት 4 ሺህ ታንኮች አንጻር ዝቅተኛ ቢመስልም ከሩስያ ጋር ጦርነት ጋር ለምትገኘው ዩክሬን አስፈላጊ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም ይላሉ የጀርመን የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ ካርል ሹልዝ።
የሀገሪቱ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ሊዮፓርድ 2 ታንክ እንዳይመረት በህግ መከልከሉም ለኬቭ መልካም ዜና አይመስልም።
አሜሪካ በበኩሏ ከ1 ኢህ በላይ ዘመናዊ ኤም 1 አብራምስ ታንክ ባለቤት ናት።
እነዚህ ታንኮች ግን የናፍጣ ፍጆታቸው በጣም ከፍተኛ ነው። ከዚህም ባሻገር በፍጥነት ጥገና ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ አለመኖሩ ኤም1 አብራምስን በኬቭ ተመራጭ እንዳይሆን አድርጎታል ነው የሚሉት ተንታኞች።