የሩሲያው ዋግነር ፖላንድን የመውረር ፍላጎት እንዳለው የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አስታወቁ
ፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ ዋግነር ወደ ምእራብ በመንቀሳቀስ ፖላንድን ለመውረር እየጠየቀ ነው ብለዋል
የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር መክረዋል
የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን አውሮፓዊቷ ሀገር ፖላንድን የመውረር ፍላጎት እንዳለው የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ የሩሲያ መንግስትና ዋግነርን ካደራደሩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በአካል ተገናኝተው መክረዋል።
በምክክሩ ወቅት ሉካሼንኮ ባደረጉት ንግግር የዋግነር ተዋጊዎች በምእራብ በኩል ወደ ፖላንድ አቅጣጫ ለመጓዝ ጥያቄ እያቀረቡ ነው ብለዋል።
የዋግነር ቡድን ወደ ዋርሳው ዘልቀን እንገባለን ማለታቸውንም ፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ ተናግረዋል።
የፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ ንግግር በቤላሩስ እና በምእራብ በኩል በምታዋስናት ፖላንድ መካከል የነበረው ውጥረት እንዲባባስ አድርጓል ነው የተባለው።
ዋግነር በሩሲያ ከፈጸመው አመጽና እሱን ተከትሎ በተደረገ ድርድርና ስምምነት ወደ ቤላሩስ መጓዙ ይታወሳል።
የቡድኑ ተዋጊዎች የቤላሩስ ወታደሮችን ሲያሰለጥኑ የሚያሳዩ ምስሎችም መለቀቃቸው አይዘነጋም።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሞስኮ በቤላሩስ እና ሌሎች ወዳጅ ጎረቤቶቿ ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በራሷ ላይ እንደተቃጣ ጥቃት ትመለከተዋለች የሚል ፖላንድን የሚያስጠነቅቅ መግለጫ ባለፈው ሳምንት ሰጥተዋል።
ይህንን ተከትሎ ስጋት የገባት ፖላንድ በርካታ ታንኮችና ወታደሮቿን ከቤላሩስ ጋር ወደሚያዋስናት ድንበር አስጠግታለች።