የሩሲያው ዋግነር ወደ አፍሪካ ሀገራት ለመዝመት እየተዘጋጀ መሆኑን ገለጸ
የቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድኑ መሪ ይቪግኒ ፕሪጎዥን ከቤላሩስ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፏል
ዋግነር ለጊዜው በዩክሬን ጦርነት እንደማይሳተፍም አስታውቋል
የሩሲያው ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ዋግነር ወደ አፍሪካ ሀገራት ለመዝመት እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ።
የቡድኑ መሪ ይቪግኒ ፕሪጎዥን በቤላሩስ ለተዋጊዎቹ ያስተላለፈበት የቪዲዮ ምስል ተለቋል።
ፕሪጎዥን ባስተላለፈው መልዕክት ተዋጊዎቹ ላስመዘገቡት ድል አመስግኖ “ለጊዜው በዩክሬን ጦርነት እንሳተፍም፤ ለአፍሪካ ጉዞ ተዘጋጁ” ብሏል።
“ወደ ዩክሬን ልንመለስ የምንችለው ራሳችን የሚያዋርድ ተግባር ውስጥ እንደማንገባ እርግጠኛ ስንሆን ነው” ሲልም ተናግሯል።
የዋግነር መሪው ተዋጊዎቹ ለአፍሪካ ጉዞ እንዲዘጋጁ ከመግለጽ ውጭ ወደየትኛው ሀገር እንደሚያመሩ ግን አልጠቀሰም።
ዋግነር ከ2018 ጀምሮ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሊቢያ እና ማሊ ተልዕኮ ወስዶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ይታወሳል።
ባለፈው ሰኞም የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንታዊ ጽህፈት ቤት የዋግነር ተዋጊዎች ከ10 ቀናት በኋላ የሚካሄደውን ህገመንግስታዊ ህዝበ ውሳኔ ሰላማዊ ለማድረግ ባንጉይ መግባታቸውን ገልጿል።
ፕሪጎዥን ትናንት በቪዲዮ የታየበት ንግግር ከአንድ ወር በፊት ቡድኑ ካካሄደው አመጽ በኋላ የሚገኝበትን ስፍራ በግልጽ ያሳየ ነው ተብሏል።
ዋግነር አመጻውን እንዲያቆም ከፑቲን ጋር ያደራደሩት የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ቡድኑ ተልዕኮውን በቤላሩስ እንደሚፈጽም መግለጻቸው አይዘነጋም።
ግለሰቡ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በክሬምሊን ተወያይቶ እንደነበር ከተገለጸ በኋ ግን ፕሪጎዢን ከቤላሩስ ወደ ሩሲያ መመለሱን ነው ሉካሼንኮ የገለጹት።
ፕሪጎዥን በትናንቱ መልዕክቱ የቤላሩስ ወታደሮችን በማሰልጠን ላይ የሚገኙት ተዋጊዎቹ ከቤላሮሳውያንን ጥንካሬን እንዲማሩና ለአፍሪካው ዘመቻ እንዲዘጋጁ አሳስቧል።