ስልጣን የተቆጣጠረው የኒጀር ወታደራዊ ቡድን የሩሲያው ዋግነር ቡድን እንዲረዳው ጠየቀ
ኢኮዋስ ጀነራል ቲያኒ ስልጣኑን ለሀገሪቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት እንዲያስረክብ የሰጠው ቀነ ገደብ ዛሬ ያበቃል
ናይጀሪያ እና ቻድ ወታደሮቻቸውን ወደ ኒጀር እንደማይልኩ አስታውቀዋል
ስልጣን የተቆጣጠረው የኒጀር ወታደራዊ ቡድን የሩሲያው ዋግነር ቅጠርረኛ ተዋጊ ቡድን እንዲረዳው ጠየቀ።
በጀነራል አብዱራህማን ቲያኒ የሚመራው የኒጀር ወታደራዊ ቡድን በኒጀር ፕሬዝዳንት ባዙም ላይ መፈንቅለ መንግሥት በመፈጸም ስልጣን መቆጣጠሩ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ወይም ኢኮዋስ ስልጣን በሀይል የተቆጣጠረው ወታደራዊ ቡድን ለቀድሞ ፕሬዝዳንት ባዙም ስልጣን እንዲመልስ አስጠንቅቋል።
ኢኮዋስ የሰጠው ቀነ ገደብም ዛሬ የሚያበቃ መሆኑን ተከትሎ በኒጀር ውጥረት ነግሷል።
ከሰሞኑ 15 አባላት ያሉት የኢኮዋስ አባል ሀገራት ወታደራዊ አዛዦች በኒጀር የተፈጸመውን መፈንቅለ መንግሥት ለመቀልበስ ወደ ኒያሚ በሚዘምቱበት ሁኔታ መክረዋል።
ስልጣን የተቆጣጠረው የኒጀር ወታደራዊ ቡድንም የኢኮዋስ አባል ሀገራት ወደ ኒያሚ ዘልቀው ቢገቡ ሀገር እንደመውረር ተቆጥሮ የአጸፋ እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የኒጀር ወታደራዊ ቡድን ወደ ማሊ በማቅናት ከሩሲያው ዋግነር ወታደራዊ ጋር መክረው ተመልሰዋል ተብሏል።
በተለይም የውጭ ሀገራት ወታደሮች ወደ ኒጀር የሚገቡ ከሆነ ዋግነር ድጋፍ እንዲያደርግ በይፋ መጠየቁ ተገልጿል።
ይህ በዚህ እንዳለ የናይጀሪያ ሴኔት የሀገሪቱ ወታደሮች ወደ ኒጀር እንዳያቀኑ በአብላጫ ድምጽ ወስኗል ተብሏል።