የሩሲያው ምናባዊ ገንዘብ ተቋም በኢትዮጵያ የዳታ ማዕከል ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ
ድርጅቱ በአዲስ አበባ ቂሊንጦ የአፍሪካ ዋና ማዕከሉን እንደሚከፍት አስታውቋል
ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት ማንኛውንም የምናባዊ መገበያያ ገንዘብ ማገዷ ይታወሳል
የሩሲያው ምናባዊ ገንዘብ ተቋም በኢትዮጵያ የዳታ ማዕከል ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ፡፡
የሩሲያው ቢት ክላስተር (ቢቲሲ) የተሰኘው ምናባዊ ገንዘብ ኩባንያ በኢትዮጵያ ማዕከሉን እንደሚከፍት አስታውቋል፡፡
ራሺያ ቱዳይ የድርጅቱን መግለጫ ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ቢቲሲ የአፍሪካ ዋና ማዕከሉን በኢትዮጵያ ለመክፈት መወሰኑን ገልጿል፡፡
በ30 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ይገነባል የተባለው ይህ የምናባዊ መገበያያ ማዕከል የፊታችን ጥር ወር ላይ እንደሚገነባም ተገልጿል፡፡
የማዕከሉ የሀይል ምንጭ ሙሉ ለሙሉ ከህዳሴው ግድብ በሚገኝ ሀይል ይሆናል የተባለ ሲሆን የምናባዊ መገበያያ ማዕከሉ ስራ ሲጀምር ኢትዮጵያን ከዓለም ቢት ኮይን ግብይት ከሚካሄድባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ያደርጋታልም ተብሏል፡፡
ቢትኮይን ... መንግስታት ምስጢራዊነትን ለምን ይጠላሉ?
ማዕከሉ በዓለም ላይ በፍጥነት እያደገ ለመጣው የምናባዊ ግብይት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ታስቦ እንደሚገነባም ተገልጿል፡፡
ይህ የምናባዊ መገበያያ ማዕከል የማይቆራረጥ እና አስተማማኝ የሀይል ምንጩን በአፍሪካ በሀይል የማመንጨት አቅሙ ትልቁ ከሆነው የህዳሴው ግድብ እንደሚያገኝ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
በዓለም ላይ ካሉ ምናባዊ መገበያያ ገንዘቦች ውስጥ ቢትኮይን ያለው ተፈላጊነት ከሌሎቹ የተሸለ ሲሆን የማዕከሉ በአዲስ አበባ መከፈት ኢትዮጵያ ተጨማሪ ገቢ እንድታገኝ ያስችላታል ተብሏል፡፡
የቢቲሲ ወደ አፍሪካ መስፋፋትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን አጋርነት ከማስፋቱ ባለፈ የአክስዮን ዋጋውን እንደሚጨምርለት ይጠበቃል፡፡
በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት የምናባዊ ግብይት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ እገዳ መጣሉ አይዘነጋም።
ባንኩ አክሎም ምናባዊ ግብይት ያልተፈቀደ እና ህገወጥ መሆኑን ጠቅሶ የዚህ ግብይት ጥቅምና ጉዳት እንዲሁም አሰራሩ ስለሚዘረጋበት ሁኔታ በቀጣይ ዝግጅት እንደሚደረግ አስታውቆም ነበር።
በፈረንጆቹ 2009 ላይ ጃፓናዊው ሶታሺ ናካሞቶ እንደተፈጠረ የሚታመነው ቢቲኮይን የተሰኘው የድጅታል መገበያያ ገንዘብ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ይህ መገበያያ ገንዘብ ዋጋው በየጊዜው ከፍ እና ዝቅ ሲል የቆየ ሲሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት ዋጋው ዝቅተኛ ምንዛሬን አስመዝግቦ ነበር።
ይሁንና በዓለም ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት እያጋጠመ ባለው የዋጋ ግሽበት እና ሌሎች የኢኮኖሚ ችግሮች ምክንያት የቢትኮይን ዋጋ እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉ ተገልጿል።