የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምዕራባውያን በሀገራቸው ላይ “ሁሉንም አይነት ጦርነት እየከፈቱ ነው”አሉ
ከሩሲያ ጎን የቆሙ ሀገራትን እንዲመዘገቡ ላቭሮቭ አቅጣጫ ሰጥተዋል ተብሏል
ቻይና እና ሕንድ የዩክሬኑ ግጭቱ እንዲቆም ቢፈገልጉም አጋርነታቸው ግን ወደ ሩሲያ አጋድሏል ተብሏል
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ሁሉንም አይነት ጦርነት እየከፈቱ መሆኑን ገለጹ፡፡
አሁን ላይ ምዕራባውያን በሚል የገለጿቸው ሀገራት የሩሲያን ኢኮኖሚ ለማጥቃት እየታገሉ ነው ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡ የተለያዩ ሀገራት ሁሉንም አይነት ማዕቀብ በመጣል የሩሲያን ኢኮኖሚ ለማጥፋ እየሠሩ ነው ሲሉ ላቭሮቭ ተናግረዋል፡፡
ምዕራባውያን እየጣሉት ያለው ማዕቀብ አላማ ያደረገው የሩሲያን ኢኮኖሚ ማሽመድመድ እንደሆነ ያነሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ሁሉንም አይነት ውጊያ መክፈታቸውን ተናግረዋል፡፡
ላቭሮቭ ይህንን የተናገሩት በሩሲያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ታዋቂ እንደሆነ ከሚጠቀሰው ጎርቻኮቭ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ፈንድ ጋር ባደረጉት ውይይት እንደሆነ የሩሲው አርቲ ዘግቧል፡፡
ምእራባውያን በአሁኑ ወቅት የጀርመኑ ሂትለር አውጆት የነበረውን አይነት ጠቅላላ ጦርነት ማወጃቸውን የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቨ ተናግረዋል፡፡
በጀርመኑ ሂትለር ሲቀነቀን የነበረው “ጠቅላላ ጦርነት” የሚለው ሃሳብ በምዕራባውያን እየተቀነቀነ እንደሆነ ላቭሮቭ አንስተዋል፡፡
ከተለያዩ ወገኖች በኩል የተጣሉት ማዕቀቦች ሩሲያን መነጠል እንዳልቻሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ብዙ ሀገራት አሁን ላይ በተመድ ቻርተር መርሆች መሰረት ከሩሲያ ጋር በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ትብብር ማድረግ እንደሚፈልጉም ላቭሮቭ አንስተዋል፡፡
ምንም እንኳን ከአሜሪካ እና አጋሮቿ ጫናዎች ቢኖርም፤ ከሩሲያ ጋር በወዳጅነት ጎራ የቆሙ ሀገራት እንዲመዘገቡ ላቭሮቭ አቅጣጫ ሰጥተዋል ተብሏል፡፡
ቻይና እና ሕንድ በጦርነቱ ምክንያት ከሩሲያ ጋር ግንኑኘት ያላቋረጡ ሀገራት መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ቤጂንግ እና ኒውዴልሂ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት እንዲያበቃና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ቢፈልጉም አጋርነታቸው ወደ ሞስኮ እንደሚያደላ ተገልጿል፡፡