ሩሲያ ፕሬዚዳንት ፑቲን በኢንዶኔዥያ በሚካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ ብላለች
ምዕራባዊያን ሩሲያን ከቡድን 20 ሀገራት የማባረር እቅድ እንዳላቸው ተገለጸ።
በኢኮኖሚ መጠናቸው ከእንደኛ እስከ 20 ባሉ ሀገራት የተመሰረተው የቡድን 20 ሀገራት ጉባኤ በቀጣዩ ህዳር ወር ላይ በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
የዚህ ቡድን አባል ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት መግቧን ተከትሎ በዚህ ጉባኤ ላይ እንዳትሳተፍ አሜሪካ እና ሌሎች የቡድኑ አባላት ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል።
ይሁንና አንድን ሀገር ከቡድኑ እንዲባረር ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ህንድ፣ ቻይና፣ ሳውዲ አረቢያ እና ሌሎች ሀገራት የግድ መስማማት አለባቸው ተብሏል።
ሩሲያ ከስምንት ዓመተ በፊት ክሪሚያን ወደ ግዛቷ መጠቅለሏን ተከትሎ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን ፣ሩሲያ እና ጣልያን አባል ከሆኑበት የቡድን ስምንት አባል ሀገራት ጉባኤ ውሰጥ መባረሯ ይታወሳል።
ከዩክሬን ጋር በገባችበት ጦርነት ምክንያት ማዕቀቦችን እያስተናገደች የምትገኘው ሩሲያ በበኩሏ ከቡድን 20 ሀገራት ጉባኤ ማንም ሊያባርረኝ አይችልም ብላለች።
በጃካርታ በሚካሄደው ጉባኤ ላይም ፕሬዘዳንት ፑቲን እንደሚሳተፉ በኢንዶኔዥያ የሩሲያ አምባሳደር ለሮይተርስ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ፕሬዘዳንት የደህንነት አማካሪ ጃክ ሱልቪያን በጉዳዩ ላይ እንደተናገሩት በቡድን 20 ላይ ሩሲያ አባል ሆና ከቀጠለች ጉባኤው የማይጠቅም ይሆናል ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ሩሲያ በዓለም አቀፍ ተቋማት እና ጉባኤዎች ላይ እንደከዚህ ቀደሙ አይሆንላትም ያሉት አማካሪው ከቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ ልትሳተፍ አትችልም ሲሉም አክለዋል።
አሜሪካ ሩሲያ በጃካርታው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ እንዳትሳተፍ እና ከቡድኑ እንድትባረር ከሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ጋር በመምከር ላይ መሆኗንም ሱልቪያን ገልጸዋል።
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የጃካርታው የቡድን 20 አገራት ጉባኤ ሩሲያን ከዚህ ቡድን ለማስወጣት በሚደረገው ውዝግብ ምክንያት የተወሰኑ አባል አገራት በጉባኤው ላይ ላይገኙ ይችላሉም እየተባለ ነው።