‘ኪንዛል’ የተሰኘ ሚሳዔልን በድጋሚ ወደ ዩክሬን ማስወንጨፏን ሩሲያ አስታወቀች
ከመቶ በላይ የዩክሬን ጦር የልዩ ኃይል አባላትንና ሌሎች ቅጥረኞችን መግደሉንም የሩሲያ ጦር አስታወቋል
ሚሳዔሉ በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙ የሃገሪቱ ጦር የነዳጅ ዴፖዎችን ዒላማ ያደረገ ነበር ተብሏል
ዛሬ እሁድ ‘ኪንዛል’ የተሰኘ ‘ሃይፐርሶኒክ’ ሚሳዔልን በድጋሚ ወደ ዩክሬን ማስወንጨፏን ሩሲያ አስታወቀች፡፡
ሚሳዔሉ በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙ የሃገሪቱ ጦር የነዳጅ ዴፖዎችን ዒላማ ያደረገ ነበር ተብሏል፡፡
ከመቶ በላይ የዩክሬን ጦር የልዩ ኃይል አባላትንና ሌሎች ቅጥረኞችን መግደሉንም የሩሲያ ጦር አስታወቋል፡፡
ወታደሮቹ ኦቭሩች ወደተሰኘች የሰሜናዊ ዩክሬን ከተማ ከባህር ላይ ባስወነጨፈው ሚሳዔል መመታታቸውንም ነው ያስታወቀው፡፡
በኪንዛል ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔል የዩክሬን ጦር ይገለገልባቸው የነበሩ የነዳጅ ዴፖዎችን ለማውደም ችያለሁም ብሏል፡፡
ዴፖው በደቡባዊ ዩክሬን ለሚንቀሳቀሰው የሃገሪቱ ጦር ወሳኝ የሎጂስቲክ አቅርቦት ጣቢያ እንደነበርም ገልጿል፡፡
ትናንት ቅዳሜም በተመሳሳይ መልኩ በምእራብ ዩክሬን የኔቶ አባል ከሆነችው ከሮማኒያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኝን የምድር ውስጥ የሚሳኤል እና ሌሎች ጦር መሳሪያዎች ማከማቻ ቦታን በ‘ኪንዛል’ ማውደሟንም ሩሲያ አስታውቃለች፡፡
ጥቃቱ ስለመፈጸሙ የዩክሬን ጦር አባላት ተናግረዋል፤ ሆኖም የትኛው የሚሳዔል ዐይነት ጥቅም ላይ እንደዋለ አላወቁም።
ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ጦርነት ሶስት ሳምንታትን ተሸግሯል፡፡ በጦርነቱ በርካታ ውድመቶች የደረሱ ሲሆን ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡