ጆ ባይደን፤ ሩሲያ ከቡድን 20 አባልነት “መሰረዘ አለባት” አሉ
ባይደን ሩሲያ የኬሚካል ጦር መሳሪያን የምትጠቀም ከሆነ አሜሪካ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነች ብለዋል
በቡድን 20 ውስጥ ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን ያላት ቻይና ሀሳቡን ተቃውማለች
ሩሲያ ከቡድን 20 አባልነቷ መሰረዝ ያለባት አሁን ነው ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ በይደን ተናገሩ።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትናንት በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃ ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ብራሰልስ ገብተው ነበር። ባይደን የአውሮፓ ጉብኝታቸውን ለማጠናቀቅ ፖላንድ መግባታቸውም ተገልጿል።
ሩሲያ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ልትጠቀም ትችላለች የሚል ስጋት በኔቶ አባል ሀገራት መካከል እንዳለ ሲገለጽ ነበር። ይሁንና ጆ ባይደን ሩሲያ የኬሚካል ጦር መሳሪያን የምትጠቀም ከሆነ አሜሪካ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነች ገልጸዋል።
“ሩሲያ ከቡድን 20 አባል ሀገርነት የምትወጣበት ጊዜ አሁን ይመስለኛል” የሚል አስተያየት መስጠታቸውም ተዘግቧል። ምንም እንኳን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ ከቡድን 20 አባልነቷ መሰረዝ እንዳለባት ቢገልጹም ቻይና ይህንን ሃሳብ ተቃውማለች። ቻይና በቡድን 20 አባል ሀገሮች ስብስብ ውስጥ ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን አላት።
የአውሮፓ ጉብኝታቸውን በፖላንድ እንደሚጨርሱ የሚጠበቁት ጆ ባይደን፤ ፖላንድ የዩክሬን ስቃይ የገባት ሀገር ናትም ብለዋል፡፡ ባይደን ፖላንድ ከዩክሬን ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ ጉብኝት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።
ዩክሬን ጎረቤቶቿ ማለትም ቤላሩስ እና ፖላንድ በተለያየ ጎራ መሰለፋች ይታወሳል። ቤላሩስ ከሩሲያ እንዲሁም ፖላንድ ከአሜሪካ ጎን ቆመው ጦርነቱን በተለያየ እይታ እየተከታተሉት መሆኑ ይታወቃል።
ጆ ባይደን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የ “ጦር ወንጀለኛ ናቸው” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን ክሬምሊን ይህ ኃላፊነት የሌለበትና ግደለሽ አስተያየት እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት በሩሲያ ላይ ተደጋጋሚ ማዕቀቦችን የጣሉ ሲሆን ኔቶ ደግሞ የአባል ሀገሮቹን “አንድ ኢንች ቦታ” እንደማያስነካ እያሳሰበ ነው።
ኔቶ ይህንን ይበል እንጅ ሩሲያ ዩክሬን የኔቶ አባል ከሆነችው ፖላንድ የምትዋሰንበትን አካባቢ በመሳሪያ ደብድባለች ተብሏል።
የዩክሬን ጦር በሩሲያ ተይዘውበት የነበሩ ቦታዎችን እያስለቀቀ መሆኑን እየገለጸ ቢሆንም ሩሲያ በበኩሏየዩክሬን ጦር የሚጠቀምበትን የነዳጅ ዲፖ መምታቷን ገልጻለች።
የቡድን 20 አባል ሀገራት 19 ሲሆኑ 20 ኛው የአውሮፓ ሕብረት ነው። ይህ ስብስብ እ.አ.አ በ 1999 የተመሰረተ ሲሆን አሜሪካን፣ ሩሲያን፣ ቻይናን፣ ደቡብ አፍሪካንና ሌሎች ሀገራትንም በአባልነት ይዟል።