አብራሪው አስከሬኑ በበርካታ ጥይት ተበሳስቶ ከመሬት ውስጥ ባለ ጋራዥ ውስጥ መገኘቱን ተገልጿል
ባለፈው አመት የጦር ጄት እያበረረ ወደ ዩክሬን የኮበለለው የሩሲያው አብራሪ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ስፔን ውስጥ ተገድሎ ተገኝቷል።
አብራሪው አስከሬኑ በበርካታ ጥይት ተበሳስቶ ከመሬት ውስጥ ባለ ጋራዥ ውስጥ መገኘቱን ሮይተርስ የዩክሬን እና ስፔን ሚዲያዎች ጠቅሶ ዘግቧል።
የስፔን መንግስት ሚዲያ(ኢኤፍኤፍ) የካቲት 13 በደቡባዊ ስፔን የተገኘው አስከሬን ኤምአይ-8 የጦር ጄት ይዞ ወደ ዩክሬን የኮበለለው የማክሲም ኩዝሚኖቭ መሆኑን ዘግበዋል።
ኩዝሚኖቭ በዩክሬን ፖስፖርት የተለያዩ ስሞችን በመጠቀም በሰፔን ይኖር እንደነበር ተገልጿል።
የዩክሬን ጂዩአር ሚሊታሪ ኢንተሊጀንስ ኩዝሚኖቭ መሞቱን አረጋግጧል፣ ነገርግን የሞተበትን ምክንያት ግልጽ አላደረገም።
የዩክሬኑ ፕራቭዳ ጋዜጣም በጥይት ተመትቶ መገደሉን ዘግቧል።
የስፔን ፖሊስ በጥይት የተገደለ አስከሬን ማግኘቱን ያረጋገጠ ቢሆንም የሟቹን ማንነት ግን ይፋ አላደረገም።
ግድያውን መጀመሪያ የዘገበው የስፔኑ "ላ ኢንፎርሜሽን ኒውስ" ጋዜጣ እንደዘገበው መሪማሪዎች ሁለት ተጠርጣሪዎችን እየፈለጉ ነው።
የዩክሬን ኢንተሊጀንስ በወቅቱ ኩዝሚኖብ ለማስከዳት መቻሉን ትልቅ ስኬት እንደሆነ ገልጾት ነበር።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ማወጇን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ሁለት አመት አልፎታል።