ጸጉሩን ሰማያዊ እና ቢጫ ቀለም የተቀባው ሩሲያዊ በቁጥጥር ስር ዋለ
የሞስኮ ነዋሪው በጸጉሩ ቀለም ምክንያት የደረሰበትን ድብደባ ሪፖርት ለማድረግ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በማምራቱ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው
ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት የሚቃወሙ ዜጎቿን የሚቀጣ ህግ ማውጣቷ ይታወሳል
በሩሲያ ጸጉሩን ሰማያዊ እና ቢጫ ቀለም የተቀባ ወጣት በቁጥጥር ስር ውሏል።
የሞስኮ ነዋሪው ስታኒስላቭ ኔቴሶቭ የዩክሬንን ሰንደቅ አለማ የሚመስል ቀለም መቀባቱ በአውቶብስ መጠበቂያ ስፍራ ባልታወቁ አካላት ድብደባ እንዲደርስበት አድርጓል።
የጸጉሩ ቀለም ስማርት ስልኩን እንዲነጠቅ እና ጥርሱም እንዲጎዳ እንዳደረገው ይናገራል።
የደረሰበት ድብደባ እና ዝርፊያ በተመለከተ ሪፖርት ለማድረግ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲያመራም ያልጠበቀው ጉዳይ እንደገጠመው ነው የገለጸው።
የጸጥታ አካላት ኔቴሶቭ የደረሰበትን ጉዳት ከመስማት ይልቅ ጸጉሩን የተቀባው ቀለም ይበልጥ ትኩረታቸውን ስቦት በቁጥጥር ስር እንዳዋሉት ተገልጿል።
ፖሊስ የወጣቱን አሻራ ተቀብሎ ተጠባባቂ ወታደሮች ወደሚመዘገቡበት ስፍራም ወስዶታል።
ሩሲያ የዩክሬንን መገለጫ ምልክቶች ማድረግና የሀገሪቱን ጦር ገጽታ የሚጎዳ ነገር መፈጸም በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ ህግ አጽድቃለች።
ኔቴሶቭም ጸጉሩን ከዩክሬን ሰንደቅ በሚመሳሰል ቀለም ለማስዋብ ሲሞክር ይህን ህግ ዘንግቶት ይሆን የመጣው ይምጣ ብሎ የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ አልጠቀሰም።
በሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ያለውን የሀገሪቱን ጦር ስም የሚያጠለሽም ሆነ የሚዋጋትን ኬቭ ከፍ የሚያደርግ ጉዳይን ፈጽሞ መገኘት እስከ 50 ሺህ ሩብል (543 ዶላር) እና እስከ አምስት አመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣል።
ባለፈው አመትም ኒኮላ ጉትሴኖቪች የተባሉ የፔንዛ ከተማ ጡረተኛ በማህበራዊ ትስስር ገጽ የሩሲያ ጦር በአሉታዊ መንገድ የተገለጸበትን ጽሁፍ በመጋራታቸው (ሼር በማድረጋቸው) 100 ሺህ ሩብል እንዲከፍሉ እንደተወሰነባቸው ዘገባዎች መውጣታቸው ይታወሳል።