800ሺ ብልቃጥ የኮሮና ክትባት ካርቱም ሲደርስ 240 ሺ ብልቃጥ ክትባት ደግሞ ሩዋንዳ ደርሷል
ሱዳንና ሩዋንዳ በድምሩ ከአንድ ሚሊዮን ብልቃጥ በላይ የኮሮና ክትባት መረከባቸውን የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት አስታወቀ፡፡
በዚህም መሰረት 800ሺ የኮሮና ክትባት ዛሬ ካርቱም ሲደርስ 240 ሺ ብልቃጥ ክትባት ደግሞ ሩዋንዳ ገብቷል፡፡ ከዚህ በፊት 4.5 ሜትሪክ ቶን የኮሮና መከላከያ ቁሳቁሶች ወደ ሱዳን ተጓጉዘው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ካርቱምና ኪጋሊ ወደ ሀገራቸው ያስገቡትን የኮሮና ክትባት ከሰሞኑ አገልግሎት ላይ ማዋል እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡ በዚህም መሰረት ለጤና ባለሙያዎች እና ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የሕጻናት አድን ድርጅት የሱዳን ተወካይ አብዱላሂ ፋድል ክትባቱ ወደ ካርቱም መግባቱ ቫይረሱ እንዳይስፋፋ እና ብዙ ህይወት እንዳይጠፋ ያግዛል ማለታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጀት ዜና ማዕከል ገልጿል፡፡
በሩዋንዳ የዩኒሴፍ ተወካይ ጁሊያና ሊንድሴይም ክትባቱ ወደ ኪጋሊ መግባቱ ታሪካዊ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ቫይረስ ለማገገም የተወሰደ የመጀመሪያ እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በሱዳን የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ኒማ ሳኢድ አቢድ ክትባቱ ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል መዳረስ እንዳለበት ገልጸው ራስን መጠበቅ ግን አሁንም አስፈላጊ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ካርቱምና ኪጋሊ የገቡት በሚሊዮን ብልቃጥ የሚቆጠሩ ክትባቶች በዓለም ጤና ድርጅት በተቀመጠውና ክትባቱን በፍትሃዊነት ለማድረስ በተወሰነው ውሳኔ መሰረት የተጓጓዙ ናቸው፡፡