ፖል ካጋሜ ሩዋንዳን በፕሬዝዳንትነት ሲመሩ 23ኛ አመታቸው ላይ ናቸው
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ስልጣን ሊለቁ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጡ።
ሩዋንዳን ላለፉት 23 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት ፖል ካጋሜ ስልጣን ሊለቁ እንደሚችሉ ተናግረዋል ።
- ሩዋንዳ ለኢትዮጵያ ችግር ውስጣዊ መፍትሄ ውጭ “ብዙም የምታደርገው የለም”፡ ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜ
- ፖል ካጋሜ ለ4ኛ ጊዜ ለሩዋንዳ ፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ ገለጹ
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ስልጣን ቢለቁ እና ጋዜጠኛ ቢሆኑ ደስተኛ ናቸው።
ሩዋንዳን እየጎበኙ ካሉት የኬንያ አቻቸው ዊሊያም ሩቶ ጋር በኪጋሉ የመከሩት ፕሬዝዳንት ካጋሜ ስለ ስልጣን መተካካት ከፓርቲያቸው ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ናቸው።
"ፓርቲዬ የእኔን ምትክ በቀጥታ ስለሚመርጥበት ሁኔት ከሚመክር ይልቅ አካታች እና ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ላይ ቢያተኩር እመርጣለሁ" ብለዋል ፕሬዝዳንት ካጋሜ።
"በቀጣይ የሚሆነውን አላውቅም፣ እንደ እኔ ፍላጎት ግን ስልጣን ለቅቄ ጋዜጠኛ ብሆን ደስተኛ ነኝ" ሲሉም አክለዋል።
የሩዋንዳ ገዢ ፓርቲ የሆነው አርበኞች ግንባር ወይም ፓትሪዮቲክ ፍሮንት ፓርቲ የመጀመሪያዋን ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት ከሰሞኑ መርጧል።
ከፈረንጆቹ 2000 ጀምሮ ሩዋንዳን እየመሩ ያሉት ፕሬዝዳንት ካጋሜ ካሳለፍነው ህዳር ወር ጀምሮ ደግሞ በተደጋጋሚ ስልጣን ስለመልቀቅ አስተያየት በመስጠት ላይ ናቸው።
ፕሬዝዳንት ካጋሜ ከወራት በፊት ከፍራንስ 24 ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በ2024 በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ እንደሚወዳደሩ ተናግረው ነበር።
ሩዋንዳ በፈረንጆቹ 2015 ላይ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ከሁለት የስልጣን ጊዜ በላይ መምራት አይችሉም የሚለውን ህግ በህዝበ ውሳኔ መሻሯ ይታወሳል።