ካጋሜ እስከ 2034 ድረስ ስልጣን ላይ መቆየት የሚያስችላቸውን ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረጋቸው ይታወሳል
ፖል ካጋሜ ሩዋንዳን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ለአራተኛ ጊዜ እንደሚወዳደሩ ገለጹ፡፡
የምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሩዋንዳ ከሁለት ዓመታት በኋላ በፈረንጆቹ 2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደምታካሂድ ይታወቃል፡፡
የወቅቱ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ለአራተኛ ጊዜ ሀገሪቱን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ካጋሜ በዚህ ምርጫ ላይ እንደሚወዳደሩ ያሳወቁት ለፈረንሳይ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ ነው፡፡
የ64 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ካጋሜ ለቀጣዮቹ 20 ተጨማሪ ዓመታት በስልጣን ላይ የመቆየት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ፖል ካጋሜ በፈረንጆቹ 2015 ላይ እስከ 2034 ድረስ በስልጣን ላይ መቆየት የሚያስችላቸውን ህግ በማውጣት በሀገሪቱ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት ያጸደቁ ሲሆን ጉዳዩ በወቅቱ ትችቶችን አስነስቶባቸው ነበር፡፡
ሩዋንዳ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጥቃት በማድረስ ላይ ያለው ኤም 23 አማጺ ቡድንን ትደግፋለች በሚል በጎረቤቷ ክስ እየቀረበባት ሲሆን ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሼስኬዲ ከሩዋንዳ ጋር ወደለየለት ጦርነት ሊገቡ እንደሚችሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ሩዋንዳ አማጺ ቡድኑን በጦር መሳሪያ፣ በደህንነት መረጃዎች እና ሌሎች ድጋፎች እየረዳች ነው የሚሉት ፕሬዝዳንት የቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሼስኬዲ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የኢኮኖሚ ፍላጎትም እንዳላት አክለዋል፡፡
የሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መሪዎች ማለትም ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሼስኬዲ እና ካጋሜ ባሳለፍነው ረቡዕ በአንጎላ መዲና ሉዋንዳ ተገናኝተው መክረዋል፡፡
በምክክሩ ፕሬዝዳንት ካጋሜ ኤም 23 የተሰኘውን አማጺ ቡድን ይረዳሉ መባሉን አስተባብለዋል፡፡ ጉዳዩ የኮንጎ የውስጥ ጉዳይ ነው እኛን አይመለከትም ሲሉም ነው ካጋሜ ክሱን ያስተባበሉት፡፡
የዲሞክራቲክ ኮንጎን የማዕድን ማወጫ መሰረተ ልማቶችን እያወደመ ያለው ኤም 23 የተሰኘው አማጺ ቡድን በሩዋንዳ እንደማይደገፍ ከዚህ በፊት ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ዲሞክራቲክ ኮንጎ ኤም 23 የተሰኘው አማጺ ቡድን ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የሩዋንዳ አየር መንገድ ወደ ሀገሯ እንዳይገባ እገዳ ጥላለች፡፡