ደቡብ ኮሪያዊው ተማሪ 160 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ሙዝ መብላቱ ተገለጸ
ተማሪው በሀገሪቱ መዲና ሲኡል ሙዝየም ውስጥ ለአውድ ርዕይ የተሰቀለ ሙዝ ነው አንስቶ የበላው
የበላው ሙዝ ይህን ያህል ገንዘብ እሚያወጣ አልመሰለኝም ያለው ተማሪው በወቅቱ ርቦኝ ነበር ብሏል
ደቡብ ኮሪያዊው ተማሪ 160 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሚየወጣ ሙዝ መብላቱ ተገለጸ።
በደቡብ ኮሪያ ስሙ ለጊዜው ያልተገለጸ የአርት ተማሪ በሚማርበት አቅራቢያ ወዳለ የአርት ጋለሪ ያመራል።
ይህ ጋለሪ በጣልያናዊው አርቲስት ማውሪዚዮ ካቴላን የተመሰረተ ሲሆን ስያሜውም ሊውም ሙዚየም ኦፍ አርት በመባል ይታወቃል።
በዚህ ሙዚየም ውስጥ ግን በግድግዳው ላይ የተሰቀለ አንድ ሙዝ አለ። የሙዚየሞቹ ጎብኚዎች ይህን ሙዝ ለመብላት ብዙ ጊዜ እንደሞከሩ ይገለጻል።
ይሁንና ለጉብኝት ወደ ሙዚየሙ ያቀናው ይህ ደቡብ ኮሪያዊ ሙዙን እንዳየ ከተሰቀለበት አውርዶ መብላቱ ተገልጿል።
በጎብኚው የተበላው ይህ ሙዝ 160 ሺህ ዶላር ወይም ከ8 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ብር ዋጋ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን ተማሪው ይህን ሙዝ ለምን እንደበላ ሲጠየቅ "ስለራበኝ በላሁት" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
"ሙዙ ያለ ምክንያት በሙዚየሙ ውስጥ እንደማይቀመጥ አውቃለሁ" ያለው ይህ ተማሪ ረሀቡ ስለጸናብኝ ልበላው ችያለሁ ሲልም ተናግሯል ተብሏል።
የሙዚየሙ ባለቤት 160 ሺህ ዶላር የሚያወጣውን ሙዝ በበላበት ጎብኚ ላይ ክስ የመመስረት ፍላጎት እንደሌለው ለሲኤንኤን ተናግሯል።
ይህ ሙዝ በሙዚየሙ ውስጥ ሲቀመጥ የራሱ የሆነ ትርጉም ይሰጣል ከመባሉ ውጪ እስካሁን ዋጋው ለምን ይህን ያህል ሊሆን እንደቻለ እና ሊተላለፍ ስለተፈለገው መልዕክት ዝርዝር ነገር አልተቀመጠም ተብሏል።