ሜሲ አርጀንቲና በታሪኳ የዓለም ዋንጫን ለሶስተኛ ጊዜ እንድታነሳ ያስቻለ ድንቅ የእግር ኳስ ጠቢብ ነው
የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን አምበልና የዓለም ዋንጫ አሸናፊው ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ በኳታር ያረፈበት ሆቴል ክፍል ወደ ሙዚየምነት እንደሚቀየር የኳታር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
በአርጀንቲና የአሸናፊነት የዓለም ዋንጫ መገባደጃ ላይ ሜሲ ከህይወት ዘመን ወዳጁና የቡድን አጋሩ ሰርጂዮ አግዌሮ ጋር ተጋርቶ እንዳረፈበት የተነገረለት ይህ ክፍል ከአሁን በኋላ እንግዶችን እንደማይቀበል የኳታር የዜና ወኪል አረጋግጧል።
አርጀንቲናዊው የፓሪስ ሴንት-ዠርመን (ፒ ኤስ ጂ) ኮከብ ተማሪዎችና ጎብኚዎች ትልቅ ትምህርት የሚወስዱበት ሙዚየም ለመድረግ መታቀዱም ነው የተገለጸው፡፡
የኳታር ዩኒቨርሲቲ የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሂትሚ አል ሂትሚ "የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲ ክፍል ሳይለወጥ ይቆያል እና ለጎብኚዎች ብቻ የሚቆይ እንጂ ለመኖሪያ አይሆንም" ሲሉ ለኳታሩ አል ሻርክ ጋዜጣ ተናግረዋል።
አክለውም "የሜሲ ንብረቶች ለተማሪዎች እና ለወደፊት ትውልዶች ውርስ እንዲሁም ሜሲ በዓለም ዋንጫው ላይ ላስመዘገበው ታላቅ ስኬት ምስክር ይሆናሉ"ም ብለዋል፡፡
ሜሲ በ2022ቱ የፍጻሜ ጨዋታ ሀገሩ አርጀንቲና ፈረንሳይን በመርታት አርጀንቲና በታሪኳ የዓለም ዋንጫን ለሶስተኛ ጊዜ እንድታነሳ ያስቻለ ድንቅ የእግር ኳስ ጠቢብ መሆኑ በርካቶች የሚመስክሩት ነው፡፡
የዓለም ዋንጫ ስኬት በማጠጣም ላይ የሚገኘው መሲ ከቀናት በፊት ከፒ ኤስ ጂ ጋር ለአንድ ዓመት መቆየት የሚያስችለውን ኮንትራት መፈራረሙ ይታወቃል፡፡
የዓለም ዋንጫ ድልን እያጣጣመ የሚገኘው የ35 አመቱ ሊዮኔል ሜሲ እስከ ጥር አጋማሽ ድረስ ወደ ፒ ኤስ ጂ ሜዳ እንደማይመለስ የክለቡ ስራ አስኪያጅ ክሪስቶፍ ጋልቲየር ገልጸዋል፡፡
ሊዮኔል ሜሲ ለፒ ኤስ ጂ 53 ጊዜ ተሰልፎ በፈረንሳይ ሊግ በሁሉም ውድድሮች 23 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል፡፡