የጅማ ሙዚየም በውስጡ “ከ2ሺህ በላይ ቅርሶች” ይዞ ይገኛል
የጅማ ሙዚየም ኢትዮጵያ ካሏት ትልቅ ታሪክ ያላቸው ሙዚየሞች ከቀዳሚዎቹ የሚጠቀስ ነው፡፡ ሙዚየሙ በውስጡ በተለይም የጅማ ወርቃማ ዘመን ተብሎ በሚጠራው ጊዜ ከ1942 እስከ 1933 ዓ.ም የተሰሩ የተለያዩ ቅርሶች ይገኙበታል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በነዚያ ዓመታት ስምንት ነገስታት ጅማን ያስተዳደሩ ሲሆን ከስምንቱ ሁለቱ አባ ጅፋሮች ናቸው፡፡
ዘመኑ የእንጨት፣ የአልባሳት፣ ብረታ ብረት እና የቆዳ ስራ ውጤቶች የተዋወቁበት የከፍታ ዘመን ነበርም ይባላል፡፡
ሙዚየሙ አሁን ያለበትን ደረጃ ላይ እንዲደደርስ የዛሬ 49 ዓመታት የተዘጋጀው የ1965ቱ የከፋ ልማት ኤክስፖ ትልቅ ሚና እንደተጫወተም ነው የታሪክ ሰነዶች የሚያመለክቱት፡፡
የጅማ ሙዚየም ተጠሪና የቅርስ ባለሙያው አቶ ነጂብ ራያ ለአል ዐይን ኒውስ እንደተናገሩት በ1965ቱ የከፋ ኤክስፖ ላይ ለእይታ የቀረቡት የጅማ ቅርሶች የወቅቱን ንጉሰ ነገስት አጼ ኃይለ ስላሴን እና የኤክስፖው ታዳሚ የነበሩትን የሆላንዷን ንግስት ጁሊያናን “ቀልብ መሳብ የቻሉ ድንቅ ቅርሶች” ነበሩ፡፡
አቶ ነጂብ የመሪዎቹን ቀልብ የገዙት ቅርሶቹ ለ1 ወር ያክል ለህዝብ ክፍት ተደርገው በህዝብ ተጎብኝተዋልም ብለዋል፡፡
ሙዚየሙ የተለያዩ ምእራፎችን ተሻግሮና ጠቅላላ ቅርሶቹ ከተሰበሰቡ በኋላ ፤ በ1972 በፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም አማካኝነት “ሙዚየም” ሆኖ በይፋ ስራውን እንደጀመረም ገልጸዋል አቶ ነጂብ፡፡
ሙዚየሙ አሁን ላይ በውስጡ ብዛት ያላቸው ቅርሶች የያዘ ተመራጭ የቱሪዝም መስህብ ሆኖ እያገለገለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
“ሙዚየሙ በውስጡ ከ2 ሺህ በላይ ቅርሶችን ይዞ ይገኛል፤ 75 በመቶ የሚሆኑ ቅርሶቹ የራሱ የአባጅፋር ሲሆኑ የተቀሩት ጅማ በከፋ ጠቅላይ ግዛት በነበረችበት ወቅት ከ6ቱ አውራጃዎች የተሰበሰቡ እንዲሁም ጣሊያን ድል ካደረግን በኋላ ሁለተኛው ወረራ ባካሄደችበት ሰአት የተሰበሰቡ የጣሊያን ቅርሶች ናቸው”ም ነው ያሉት የቅርስ ባለሙያው አቶ ነጂብ ራያ፡፡
ከሙዚየሙ ቅርሶች አብዛኞቹ ከ100 እስከ 120 ዓመታት ያስቆጠሩ ናቸው ያሉት አቶ ነጂብ አብዛኞቹ ከቆዳ የተሰሩ፣ ከግዙፍ ግንድ የተፈለፈሉ የእንጨት ውጤቶች፣ አልባሳት፣ የቀንድ ውጤቶች፣ የብርታ ብረት እና መሰል ውጤቶች መሆናቸውም ተናግረዋል፡፡
ሙዚየሙ ከመንግስት በዘለለ አkaባቢው ባለው ማህበረሰብ አስፈላጊው እንክብካቤ እንደሚደረግለትም ነው ባለሙያው የገለጹት፡፡
“ማህበረሰቡ ማንነቱን፣ ባህሉንና ያሳለፈውን ታሪክ ለትውልድ ያስተላልፍልኛል የሚል አመለካከት ስላለው ለሙዚየሙ አስፈላጊውን እንክብካቤ ሁሉ በማድረግ ላይ ነው” ም ብለዋል፡፡