ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገሪቱ ከተጋረጠባት ውስብስብ ችግሮች እንደሚያወቷት ገልጸዋል
ሳዕድ ሀሪሪ በድጋሚ የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ
ሊባኖስን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ሳዕድ ሀሪሪ በድጋሚ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ሀሪሪ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታን ሲይዙ የአሁኑ አራተኛቸው ነው፡፡
የቀድሞው የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሰን ዲያብ ሊባኖስ ከአስርት ዓመታት ወዲህ ካጋጠማት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና በቤይሩት ካጋጠማት ከፍተኛ ፍንዳታ ጋር ተደምሮ በገጠማት ለወራት የዘለቀ የፖለቲካ ቀውስ ሳቢያ የደረሰባቸውን ጫና ተከትሎ በገዛ ፈቃዳቸው ነበር ከመሪነት የተነሱት፡፡
ሐሙስ ዕለት የሊባኖስ የፓርላማ አባላት በጠባብ ልዩነት ከስልጣን ከተነሱ ከዓመት በኋላ ሀሪሪ በድጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንዲሰየሙ እና አዲስ ካቢኔ እንዲያቋቁሙ ተስማምተዋል፡፡
ተመራጩ ሀሪሪም በአፋጣኝ ካቢኔ እንደሚያዋቅሩ ገልጸው የምጣኔ ሀብትና የፋይናንስ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርጉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም በርካታ የሊባኖስ ዜጎች የሀገሪቱ የተወሳሰበ ችግር በአዲሱ መሪያቸው ይፈታል ብለው እንደማያምኑ እየተዘገበ ነው፡፡
ሳዕድ ሀሪሪ መላው ሊባኖሳውያን ከገጠማቸው ችግርና ሀገሪቱ ከተደቀነባት አደገኛ መስመር እንድትወጣ እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል ቢቢሲ እንደዘገበው፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሊባኖስ ደርሶ በነበረው ፍንዳታ ለማጽናናት እና ለጉብኝት ሁለት ጊዜ ወደ ቤሩት ያቀኑ ሲሆን ለሀገሪቱ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ገቢ ከማሰባሰባቸውም ባለፈ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ማሻሻያ የፈረንሳይ ድጋፍ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሳዕድ ሀሪሪ እ.ኤ.አ. በ2017 ህዳር ወር ላይ ሂዝቦላህ እና ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ የሚፈጥሩትን ቀውስ በመቃወም እና ለህይወታቸው በመስጋት ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቅንተው ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን አሳውቀው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከ2 ሳምንት በላይ ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ከፕሬዝዳንቱ ጋር በመማከር ከኃላፊነት የመነሳታቸውን ጉዳይ ማቆየታቸውን መግለጻቸው በወቅቱ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡