የሀገሪቱ ቀጣይ እጣፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
የሊባኖስ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ስልጣን ለቀቀ
በሊባኖስ መዲና በቤሩት ከተከሰተው ከፍተኛ ፍንዳታ በኋላ ህዝባዊ የአደባባይ ተቃውሞ የበረታበት የሊባኖስ መንግስት በፈቃዱ ከኃላፊነት ወርዷል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሳን ዲያብ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው መንግሥታቸው ስልጣን ለማስረከብ መወሰኑን አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት፣ ለተከታታይ ቀናት የተካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ፣ የተለያዩ ሚኒስትሮች እና ሌሎች ባለስልጣናት የስልጣን መልቀቂያ ካስገቡ በኋላ ነው።
የመንግሥት ተቃዋሚዎች የሀገሪቱ ባለስልጣናት በሀገር ጉዳይ ቸልተኞች እና በሙስና የተተበተቡ መሆናቸውን በመግለጽ መንግሥትን ይወነጅላሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በንግግራቸው ይህን ውንጀላ ተቀብለዋል። በሊባኖስ ሙስና ከሀገሪቱ ከራሷ በላይ የገዘፈ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዲያብ ይህም ለውጥ እንዳናመጣ አድርጎናል ብለዋል።" እኛ ብቻችንን ነበርን እነርሱ ደግሞ ሁሉም (ሙሰኞቹ ) ከእኛ በተቃራኒ ናቸው" ሲሉም ፈታኝ ጊዜ ማሳለፋቸውን ገልፀዋል።
አል አረቢያ እንደዘገበው የጠቅላይ ሚኒስትሩን እና እርሳቸው የሚመሩትን የሀገሪቱ መንግሥት ካቢኔ ከስልጣን የመውረድ ጥያቄ የተቀበሉት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሚሼል አውን፣ አዲስ መንግሥት እስኪመሰረት ተሰናባቹ መንግሥት ሀገሪቱን በአደራ እንዲያስተዳድር ጠይቀዋል።
የመንግስት መልቀቅ መንስኤ-የቤይሩት ፍንዳታ እና የሀገሪቱ ቀውስ
ሀገሪቱ ከገባችበት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር ተያይዞ።፣ የቤይሩት ፍንዳታ ከመከሰቱም በፊት የሊባኖስ ህዝብ ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ ለወራት አደባባይ በመውጣት መንግሥትን ሲቃወም እና የስርዓት ለውጥ ሲጠይቅ ቆይቷል።
አስቀድሞም በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ሊባኖስ የተከሰተው ፍንዳታ የሀገሪቱን ችግር ይበልጥ አወሳስቧል። ፍንዳታው 220 ሰዎችን ለህልፈት መዳረጉን የቢቢሲ ዘገባ የሚያሳይ ሲሆን 110 ሰዎችም የሚገኙበት እንደማይታወቅ አስነብቧል። ከ6 ሺ በላይ ሰዎችም በፍንዳታው ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የፍንዳታው ምክንያት ለዓመታት በወደቡ ተከማችቶ የቆየ 2ሺ 75, ቶን የሚመዝን አሞኒየም ናይትሬት መሆኑ ይታወቃል። ፍንዳታው 6 ሺ ህንጻዎችን ያወደመ ሲሆን ይህም ወደ 300 ሺ የሚደርሱ ሰዎችን በቤሩት ቤት አልባ አድርጓቸዋል።
አጠቃላይ በፍንዳታው የደረሰው የጉዳት መጠን 3 ቢሊዮን ዶላር የተገመተ ሲሆን ለመልሶ ግንባታ 15 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል።
የሊባኖስ ቀጣይ እጣፈንታ
የሀገሪቱ ፖለቲካና አስተዳደር ሙስና ውስጥ ክፉኛ መዘፈቁ ፍንዳታውን እንዳስከተለ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሳን ዲያብ የሥልጣን መልቀቂያ ንግግር ባደረጉበት ወቅት አስታውቀዋል።
ይህም የተወሰኑ ግለሰቦች የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የፈጸሙት ድርጊት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኬሚካሉ ለሰባት ዓመታት በወሰቡ ተደብቆ እንዲቆይ ያደረጉ ግለሰቦች ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለረጅም ዓመታት በሙስና የተተበተበውን አስተዳደር ሪፎርም በማድረግ ላይ እንደነበሩም በንግግራቸው አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ ምክር ቤት በቅርቡ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሰይም ይጠበቃል።
ይሁንና ሀገሪቱ ካለችበት ውስብስብ የፖለቲካ ስርዓት አንጻር ሲታይ ምክር ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት ከባድ ፈተና እንደሚጠብቀው ይታመናል።
በተለይ በሊባኖስ የሀገሪቱን ስልጣን የተጋሩ አካላት ከተለያየ ሃይማኖት በስሌት የተካተቱ መሆናቸው የምክር ቤቱ ዋነኛ ፈተና ይሆናል ተብሏል።
በተጨማሪም ከአውሮፓውያኑ 1975 እስከ 1990 የቆየው የሀገሪቱ የእርስበርስ ጦርነት ሲያበቃ በርካታ የጦር አበጋዞች ወደ ፖለቲካው ገብተው እስካሁንም አብዛኛውን የሀገሪቱን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዘርፎች መቆጣጠራቸው ነገሮችን ይበልጥ እንደሚያወሳስብ ይጠበቃል። ይህም ህዝቡ የፈለገው ለውጥ የምጣቱን እና ሀገሪቱ ከገጠማት ሁለንተናዊ ቀውስ አገግማ ወደ መረጋጋት የመመለሷን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ያስገባ አጣብቂኝ ሆኗል።