በሀገሪቱ የስርዓት ለውጥ እንዲደረግ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ በመጠየቅ ላይ ናቸው
በሊባኖስ ቤሩት ህብረተሰቡ መንግስትን ለመቃወም አደባባይ ወጣ
በትንሹ 145 ሰዎች የሞቱበት እና ከ5,000 በላይ ሰዎች የተጎዱበት የቤሩት ፍንዳታ ህብረተሰቡ ለተቃውሞ አደባባይ እንዲወጣ አድርጓል፡፡ ትናንት ምሽት የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ላይ የሚገኙ ሰዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል፡፡ ሰልፈኞቹ በፖሊስ ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስ ለመበተን ሞክሯል፡፡
ፍንዳታው መንግስት የሀገሪቱን ችግሮች ለመፍታት አቅም አልባ የመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ተቃዋሚዎች በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሀገሪቱ ባለስልጣናት በሙስና ስለመዘፈቃቸው የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ያነሳሉ፡፡
በትናንትናው እለት በቤሩት ፍንዳታው በተከሰተበት አካባቢ ጉብኝት ያደረጉት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኤማኑኤል ማክሮን ቀድሞውንም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ዉስጥ የምትገኘውን ሊባኖስን ለመደገፍ በቀናት ዉስጥ ዓለም አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብር እንደሚካሔድ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅትም በመንግስት ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ ሰዎች ፈረንሳይ በሊባኖስ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡
ለሰልፈኞቹ “ቁጣችሁን ተረድቻለሁ ፤ መንግስትን ሳይሆን ህዝቡን ለመደገፍ ነው የመጣሁት” ያሉት ፕሬዝዳንት ማክሮን በሀገሪቱ ጥልቅ የፖለቲካ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ “ለሀገሪቱ የምንሰጠው ድጋፍ በሙሰኞች እጅ እንደማይወድቅ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በሊባኖስ አዲስ የፖለቲካ ስርዓት እንደሚያስፈልግም ነው ማክሮን የተናገሩት፡፡
ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ 16 ሰዎች መታሰራቸውን የሊባኖስ ዜና ወኪል አስታውቋል፡፡ ሁለት የመንግስት ባለስልጣናትም ከኃላፊነት ተነስተዋል፡፡
በቤሩት ወደብ በተከሰተው ከፍተኛ ፍንዳታ የወደመው ሀብት 5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት የሀገሪቱ ባለስልጣናት ያሳወቁ ሲሆን ስፍራውን መልሶ ለመገንባት 15 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደሚያስፈልግም የ ዘ ናሺናል ዘገባ ያመለክታል፡፡ ፍንዳታው 300,000 ያህል ሰዎችን ቤት አልባ እንዲሆኑም አድርጓል፡፡