ፍንዳታው የተከሰተው በቤይሩት ወደብ 200 ገደማ ሰዎች የሞቱበት ፍንዳታ ከተከሰተ ከ 7 ሳምንታት በኋላ ነው
በሊባኖስ በሂዝቦላህ የመሳሪያ መጋዘን ውስጥ ፍንዳታ ተከሰተ
በሊባኖስ በሚገኘው የሂዝቦላህ የመሳሪያ መጋዘን ዛሬ ማክሰኞ በቴክኒካዊ ስህተት ምክንያት ፍንዳታ መከሰቱን የሀገሪቱ ደህንነት ምንጭ አስታወቀ፡፡
የሂዝቦላህ ጠንካራ ይዞታ በሆነው በደቡባዊ ሊባኖስ የተከሰተው ፍንዳታ አካባቢውን ያናወጠ ሲሆን በስፍራው ከፍተኛ ጭስ እየጨሰ ነው፡፡
ፍንዳታው የተከሰተው ከወደብ ከተማዋ ከሲዶን ከፍ ብላ በምትገኘው በአይን ቃና ደቡባዊ መንደር ነው፡፡
ፍንዳታው ስላደረሰው ጉዳት እስካሁን የወጣ መረጃ አልተገኘም፡፡
አንድ የሊባኖስ የሂዝቦላህ ባለስልጣን ፍንዳታ መኖሩን አረጋግጠው ነገር ግን ተጨማሪ ዝርዝሮችን ከመስጠት ተቆጥበዋል ፡፡
የሂዝቦላህ ቡድን አባላት ጋዜጠኞች ወደ አካባቢው እንዳይደርሱ በማገድ የፀጥታ ስራ ማከናወን ጀምረዋል፡፡
በአከባቢው አል ጃዲድ ጣቢያ የተላለፈው የቪዲዮ ቀረፃ በህንፃዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ያሳያል፡፡
የአሁኑ ፍንዳታ የተከሰተው በቤይሩት ወደብ በአሞኒየም ናይትሬት ክምችት ከፍተኛ ፍንዳታ ከተከሰተ ከሰባት ሳምንታት በኋላ ነው፡፡ በቤይሩቱ ፍንዳታ 200 ገደማ ሰዎች ሲሞቱ 6,500 ያህል ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡