የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መንግስት የደቡብ ሱዳን ክልሎች 10 እንዲሆኑ ወሰነ
የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መንግስት የደቡብ ሱዳን ክልሎች 10 እንዲሆኑ ወሰነ፡፡
በአውሮፓውያኑ መስከረም 12/2018 በአዲስ አበባ ከተደረሰው ስምምነት ወዲህ ለሁለት ጊዜያት የተራዘመው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ጉዳይ አሁንም እልባት አላገኘም፡፡
የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች በሀገሪቱ ክልሎች እና ብሔራዊ ጦር ላይ ከመግባባት ደርሰው የሽግግር መንግስት እንዲመሰርቱ የተሰጣቸው የመጨረሻው ተጨማሪ 100 ቀን ሊጠናቀቅ ከዛሬ የካቲት 10 በኋላ 4 ቀን ብቻ ቀርቷቸዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጡት በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን፣ ለሰላም ሲባል 32 የነበሩት የሀገሪቱ ክልሎች ወደ 10 ዝቅ እንዲሉ መንግስት መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከአሁን ቀደም የነበሩት ሶስት ግጭት ያለባቸው አስተዳደራዊ ግዛቶች ማለትም ግሬተር ፒቦር፣ አቢዬ እና ርዌንግ አደረጃጀታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በሽግግሩ ወቅት በፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ስር ይቀጥላሉ፡፡
አምባሳደሩ እንዳሉት ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 7 የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ሁለቱ ምክትሎቻቸው፣ ብሔራዊ የሽግግር መንግስት ሳይመሰረት የተጨመረው 100 ቀን እያለቀ በመሆኑ፣ በሀገሪቱ ያለውን ሁኔታ በአጽንኦት ለመገምገም ተገናኝተዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኪር የደቡብ ሱዳን ህዝብ ስቃይ እንዲያበቃ በማሰብ ከምክትሎቻቸው ጋር በደረጉት ውይይት፣ 32ቱ ክልሎች ፈርሰው ቀድሞ የነበሩት 10 ክልሎች እንዲደራጁ መስማማታቸውንም አምባሳደሩ በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡
የህዝቡ ፍላጎት 32ቱ ክልሎች ቢሆኑም ለሰላም ሲባል ወደቀድሞው አደረጃጀት እንዲመለስ ውሳኔው ተላልፏል ነው ያሉት አምባሳደር ሞርጋን፡፡ የመንግስት ተቀናቃኞች ክልሎቹ ከ21-24 እንዲሆኑ ይፈልጋሉ፡፡
አሁን መንግስት የወሰነው የ10 ክልል የመፍትሔ ሀሳብ ሀገሪቱ ነጻ ከመውጣቷ በፊት በቀድሞው የሱዳን መሪ ኦማር ሀሰን አልበሽር ዘመነ መንግስት የነበረ አወቃቀር ነው፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ ዛሬ፣ የሱዳንና ዩጋንዳ መሪዎች የሚሳተፉበት ውይይት በጁባ እንደሚደረግም ነው አምባሳደሩ በመግለጫቸው ያነሱት፡፡
የተቀናቃኞቹ ዋነኛው ያለመግባባታቸው ምክኒያት፣ የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መንግስት የሀገሪቱ ክልሎች 32 ሆነው እንዲቀጥሉ የሚፈልግ ሲሆን ሪክ ማቻርና አጋሮቹ 24 ወይም 21 እንዲሆኑ መፈለጋቸው ነው፡፡
አምባሳደሩ የመንግስት ተቀናቃኞችን ከጦርነት በመላቀቅ ሰላም እንዲሰፍን አይፈልጉም ሲሉ ተችተዋቸዋል፡፡
የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች በክልሎች ቁጥር ላይ ተግባብተው የሽግግር መንግስት ለመመስረት የተሰጣቸው 100 ቀን የካቲት 14 ያበቃል፡፡
በቀሪዎቹ ቀናት በተቀናቃኞቹ መካከል ስምምነት ከተደረሰ ለ30 ወራት የሚቆይ የሽግግር መንግስት ይመሰረታል ነው የተባለው፡፡