ሳውዲ አረቢያ እየጨመረ የመጣውን የቻይና የነዳጅ ፍላጎትን የመሙላት ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች
ሳውዲ አረቢያ ከቻይና ጋር የበለጠ መተባበር እንደምትፈልግ ገለጸች፡፡
ሳውዲ አረቢያ ከምንግዜም ተቀናቃኟ ኢራን ጋር በቻይና አደራዳሪነት ወደ ስምምነት የመጣች ሲሆን ከቤጂንግ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማጥበቅ እንደምትፈልግ አስታውቃለች፡፡
የሳውዲ አረቢያ የሀይል ሚኒስትር ለቪኦኤ እንዳሉት ከቻይና ጋር መወዳደር ሳይሆን የትብብር አጀንዳዎችን ማጠናከር የሪያድ ፍላጎት ነው ብለዋል፡፡
ሪያድ ግንኙነቷን ከቻይና ጋር ማጥበቋን ተከትሎ ከምዕራባዊያን ሀገራት የመጠራጠር ስሜት እያደገ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ይህ ግን ሳውዲን አያሳስብም ማለታቸው ተገልጿል፡፡
የዓለማችን ቀዳሚ ነዳጅ ሻጭ ሀገር የሆነችው ሳውዲ አረቢያ ነዳጅን በመሸመት ከዓለም ሀገራት መካከል ቀዳሚ ከሆነችው ቻይና ጋር ከንግድ ባለፈ በብዙ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በተለይም በጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮችም በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን ቻይናን በጠላትነት የፈረጁት ምዕራባዊያን ሀገራት የሀገራቱን ግንኙነት በመጠራጠር ላይ ናቸው ተብሏል፡፡
የሳውዲ አረቢያ የሀይል ሚኒስትር ልዑል አብዱል አዚዝ ቢን ሳልማን በዚህ ጉዳይ ላይ በተጠየቁበት ወቅት እንዳሉት ለምዕራባዊያን መጠራጠር ምላሽ ያለንም፣ ቢዝነስ ቆሞ አይጠብቅህም ቢዝነሱ ወዳለበት በነጻነት እንንቀሳቀሳለን ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
"የምዕራባዊያን ሀገራት ከእኛ ጋር ናችሁ ወይስ ከማን ጋር ናችሁ እያሉ ይጠይቁናል” የሚሉት ሚኒስትሩ ሪያድ ከማንኛውም ሀገር ጋር ጥቅሟን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ትመሰርታለች ሲሉም አክለዋ፡፡
ቻይና የሳውዲ አረቢያ ዋነኛ ነዳጅ ገዢ ሀገር ስትሆን ሁለቱ ሀገራት በዩዋን ለመገበያየትም መስማማታቸው ተገልጿል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም የቻይና የነዳጅ ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፣ ይህን ፍላጎት ደግሞ እኛ ለመሙላት እየሞከርን ነው እኛ ከማንም ሀገር ጋር እየተፎካከርን አይደለም ብለዋ፡፡