ኢራን እና ሳውዲ አረቢያ ከሰባት ዓመታት በኋላ ግንኙነታቸውን ለማስተካከል ተስማምተዋል
ኢራን እና ሳዑዲ አረቢያ ከሰባት ዓመታት ባላንጣነት በኋላ ግንኙነታቸውን ለማደስ ተስማምተዋል።
የሀገራቱ መቃቃር በባህረ ሰላጤው ላይ መረጋጋትን እና ደህንነትን አደጋ ላይ የጣለ እና በመካከለኛው ምስራቅ ከየመን እስከ ሶሪያ ያለው ግጭት እንዲባባስ አድርጓል ተብሏል።
ስምምነቱ ይፋ የተደረገው በሁለቱ ተቀናቃኝ የመካከለኛው ምስራቅ ኃይሎች ከፍተኛ የጸጥታ ኃላፊዎች መካከል ከቀናት በፊት በቤጂንግ ሚስጥራዊ ውይይት ከተደረገ በኋላ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ቴህራን እና ሪያድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለመቀጠል ኤምባሲዎቻቸውን በሁለት ወራት ውስጥ ለመክፈት መስማማታቸውን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
መግለጫው "ስምምነቱ የሀገራቱን ሉዓላዊነት መከበር እና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባትን የሚያጠቃልል ነው" ብሏል።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሳዑዲ አረቢያ ኢራን በነዳጅ ፋብሪካዎቿ ላይ የሚሳይልና የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ፈጽማለች በሚል ስትከስ ከርማለች።
ኢራን ደግሞ ክሱን አስተባብላለች።
የየመን ከኢራን ጋር የተቆራኘው የሁቲ አማጺ የሚሳይልና ሰው አልባ ጥቃቶችን፤ ሁቲን የሚዋጋውን ጥምረት በምትመራው በሳዑዲ አረቢያ ላይ አድርሷል።
የኢራን ከፍተኛ የጸጥታ ባለስልጣን አሊ ሻምካኒ እና የሳዑዲ አረቢያ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሙሳድ ቢን መሀመድ አል-አይባን የተፈራረሙት ስምምነት፤ በ2001 የተፈረመውን የጸጥታ ትብብር ስምምነት እንዲሁም ቀደም ብሎ በንግድ፣ ኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት ላይ የተፈረመውን ስምምነት እንደገና እንዲጀመር ያዛልም ነው የተባለው።
የቻይናው ከፍተኛ ዲፕሎማት ዋንግ ዪ ስምምነቱ የሰላም ድል መሆኑን ገልጸው፤ ቤጂንግ ጠንካራ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ለመፍታት ገንቢ ሚናዋን ትቀጥላለች ብለዋል።
የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ አሜሪካ ስለስምምነቱ እንደምታውቅ እና በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ውጥረት ለማርገብ የሚደረገውን ማንኛውንም ጥረት በደስታ እንደምትቀበል ተናግረዋል።