ሳኡዲ አረቢያ ለፕሬዝዳንት አላሳድ ያደረገችው አቀባበል ለአሜሪካ ግልጽ መልዕክት ማስተላለፉ ተገለጸ
ሳኡዲ አረቢያ ያለአሜሪካ አጋዥነት በራሷ መቆም እንደምትችል በማሳየት ላይ ናት ተብሏል
ሶሪያ ከ12 ዓመታት በኋላ በሪያድ ጥረት ወደ አረብ ሊግ ተመልሷል
ሳኡዲ አረቢያ ለፕሬዝዳንት አላሳድ ያደረገችው አቀባበል ለአሜሪካ ግልጽ መልዕክት ማስተላለፉ ተገለጸ።
የዓለማችን ዋነኛ የነዳጅ አቅራቢ ሀገር የሆነችው ሳኡዲ አረቢያ ላለፉት ዓመታት የዲፕሎማሲ መካረር ውስጥ ከገባችባቸው ሀገራት ጋር ወዳጅነቷን በማሻሻል ላይ ትገኛለች፡፡
ሀገሪቱ የመካከለኛው ምስራቅ የበላይነትን ለመቆጣጠር ከአሜሪካ ጋር በመተባበር ከኢራን፣ ኳታር እና ሌሎችም ሀገራት ጋር የተበላሸ ግንኙነት ነበራት፡፡
የሳውዲው አልጋወራሽ ልዑል መሀመድ ቢን ሳልማን ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ከአሜሪካ ጋር ያለው ወዳጅነት እየሻከረ መምጣቱ እየተገለጸ ይገኛል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የበለጠ እየተሸረሸረ የመጣው አሜሪካ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ልዑል መሃመድ ቢን ሳልማን ቀጥተኛ ትዕዛዝ ተገድለዋል የሚል አቋም ከያዘችበት ጊዜ ጀምሮ ነው ተብሏል፡፡
ይህንን ተከትሎም ልዑል መሀመድ ቢን ሳለማን ሳኡዲ አረቢያ ያለ አሜሪካ አጋዥነት በራሷ ዲፕሎማሲዋን መቀጠል እንደምትችል ማሳየት ይፈልጋሉ ተብሏል፡፡
ሮይተርስ የገልፍ ጥናት ማዕከል ሊቀመንበር የሆኑት አብዱላዚዝ አል ሳገርን አነጋግሮ በሰራው ዘገባ ልዑል መሀመድ ቢን ሳልማን ሀገራቸው ከዚህ በፊት ቁርሾ ውስጥ ከነበሩት ሀገራት ጋር ግንኙነታቸውን በማደስ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
በቅርቡም የሶሪያውን ፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ ከ12 ዓመት መገለል በኋላ ወደ አረብ ሊግ እንዲመለሱ ማድረጋቸው ለዋሸንግተን መልዕክት ማስተላለፋቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡
ሳኡዲ አረቢያ ከምንጊዜም ተቀናቃኟ ኢራን ጋር በቻይና አሸማጋይነት ግንኙነቷን ማደሷ፣ ከኳታር ጋርም ተመሳሳይ የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን ማደሷ ሪያድ ያለ አሜሪካ እርዳታ በራሷ መቆም እንደምትችል በማሳየት ላይ እንደሆነችም ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል፡፡
ሳኡዲ አረቢያ የመካከለኛው ምስራቅ የሀይል የበላይነትን በመቆጣጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት በማሳየት ላይ መሆኗም ተገልጿል፡፡