ሳዑዲ አረቢያ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ለመመስረት ቅድመ ሁኔታ አስቀመጠች
እስራኤል ከአረብ ሀገራት ጋር የደረሰችው ስምምነት ከፍልስጤም ጋር እንድትደራደር በር ከፋች ነው ብለዋል
ምስራቅ ኢየሩሳሌምን ዋና ከተማ ያደረገ የፍልስጤም መንግስት መመስረት እንዳለበት የሳዑዲ ውጭ ጉ/ሚኒስትር ገልጸዋል
የሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፈይሰል ቢን ፋርሃን ቢን አብዱላሂ እንዳሉት በሳዑዲ አረቢያ እና በእስራኤል መካከል ሰላም የሚሰፍነው ምስራቅ ኢየሩሳሌምን ዋና ከተማ በማድረግ የፍልስጤም መንግስት ሲመሰረት ነው፡፡
ከአል አረብያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በእስራኤል መካከል የሰላም ስምምነት መች ሊፈረም እንደሚችል ለቀረበላቸው ጥያቄ ቢን ፋርሃን ሲመልሱ ይህ ጉዳይ “በአረብ የሰላም ኢኒሼቲቭ መሠረት ምስራቅ ኢየሩሳሌም ላይ ዋና ከተማውን ከደረገ የፍልስጤም መንግስት ምስረታ እና ከፍልስጤም ጋር በሚደረስ የሰላም ስምምነት ላይ የሚመሰረት ነው” ብለዋል፡፡
የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፣ ሀገራቸው ከእስራኤል ጋር የሚኖራትን ግንኙነት ለመወሰን ‘የአረብ የሰላም ኢኒሼቲቭ’ ዋናው ርዕስ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
በቅርቡ በአረብ ሀገራት እና በእስራኤል መካከል የተደረሱትን የሰላም ስምምነቶች በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “በዋነኛነት ለሰላም ሂደቱ እና ሁላችንም የምንፈልገውን ዋና ከተማዋ በምስራቅ ኢየሩሳሌም የሆነ የፍልስጤም መንግስት የለማሳካት አዎንታዊ ተፅእኖ ይኖራቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፈይሰል ቢን ፋርሃን ፣ በተጨማሪም የሰላም ስምምነቶቹ እስራኤል ለዚህ ጉዳይ የመጨረሻ መፍትሄ ለመስጠት እና ፍትሃዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ ከፍልስጤማውያን ጋር ጠንካራ ድርድር እንድታደርግ እንደሚያነሳሷት ገልጸዋል፡፡
እስራኤል ከወራት በፊት ከዩኤኢ ጋር የሰላም ስምምነት ላይ የደረሰች ሲሆን በማስከተልም ከባህሬን እና ከሞሮኮ ጋር ሰላም አውርዳለች፡፡ ከሱዳንም ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ሀገሪቱ አብዛኛውን መንገድ ጨርሳለች፡፡