አቡዳቢ፣ቴላቪቭ እና ዋሸንግተን የጋራ ፈንድ ለመመስረት መስማማታቸው ተገለጸ
አቡዳቢ፣ቴላቪቭ እና ዋሸንግተን የጋራ ፈንድ ለመመስረት መስማማታቸው ተገለጸ
አብርሃም ፈንድ በሚል ሥያሜ የሚቋቋው ይህ ፈንድ መቀመጫውን በእየሩሳሌም እንደሚያደርግም ነው የተገለጸው፡፡ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችና እስራኤል ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከመሰረቱ በኋላ አብርሃም ስምምነት እየተባለ ከሚጠራው ስም አብርሃም ፈንድ የሚለውን ወስዷል፡፡
ፈንዱ በ3 ቢሊዮን ዶላር የሚቋቃም ሲሆን በመካከለኛው ምሥራቅና በሰሜን አፍሪካ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እና የኢኮኖሚ ትብብርን ለማጠናከር የታለመ ነው ተብለዋል፡፡
የዚህ ፈንድ መቋቋም የሶስቱ ሀገራት ወዳጅነትና ትብብር በአዲስ መንፈስ ማደጉን የሚያመለክት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የሶስቱ ሀገራት የጋራ ትብብር ቀጠናውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጠቅመው በእስራኤል የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡
ሕዝብም መሰረት ያደረገ ኢንቨስትመንት ነው የተባለው ይህ ፈንድ የቀጣናውን ንግድ፣ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች፣የሃይል አቅርቦት፣ጸጥታና እርሻን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚግዝ ነው የተገለጸው፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ለትውልዶች የሚሆን ታሪክ እየሰራን ነው ሲሉ ይህንን ሶስቱ ሀገራት ያቋቋሙትን ፈንድ አድንቀዋል፡፡ ይህ የሶስቱ ሀገራት ወዳጅነት መላው ዓለም ከወዳጅነት፣ ከጤናማ ግንኑነትና ከሰላም ብዙ መጠቀም እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስትር ስቲቭ ምኑችን በበኩላቸው የተቋቋመው ፈንድ በመካከለኛው ምስራቅ የዳበረ ኢኮኖሚ ያላቸው የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችና እስራኤል ቀጥታ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ያሳያል ብለዋል፡፡