ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ እስራኤልና ሞሮኮ ግንኑነት ለመጀመር መስማማታቸውን አደነቁ
የዩኤኢው ሼክ መሓመድ የሞሮኮው ንጉስ መሐመድ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ተስማምተዋል
አሜሪካ ለሞሮኮ ሉአላዊነት የሰጠችውን እውቅናም ሼክ መሐመድ አድንቀዋል
የአቡዳቢ ልዑል አልጋወራሽ እና የዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን እስራኤልና ሞሮኮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር መስማማታቸውን አደነቁ፡፡
ልዑል አልጋ ወራሹ ከሞሮኮው ንጉስ መሐመድ 6ኛ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ቴላቪቭና ራባት ግንኙነት ለማድረግ መወሰናቸውን አድንቀዋል፡፡ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አሜሪካ ምዕራባዊ ሳሃራ የሞሮኮ ሉዓላዊ ግዛት አካል ለመሆኗ ዕውቅና መስጠቷም የሚመሰገንና በበጎ የሚታይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ሼክ መሐመድ ቢንዛይድና ንጉስ መሐመድ 6ኛ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን የሞሮኮው ንጉስ መሐመድ 6ኛ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ሞሮኮ ያላቸው ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸው ተጠቁሟል፡፡
የአቡዳቢ ልዑል አልጋወራሽ እና የዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ፣ አሜሪካ ለሞሮኮ ሉዓላዊነት የሰጠችው እውቅና የሚመሰገን እንደሆነ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡ የእስራኤልና የሞሮኮ ግንኑነት መጀመርም ለቀጣናው ሰላም፣ ብልጽግናና መረጋጋት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑንም ነው የገለጹ፡፡
የሞሮኮው ንጉስ መሐመድ 6ኛ የዩኤኢው ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ለሞሮኮ ለሚያደርጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ቴላቪቭና ራባት ግንኑነት ለመጀመር የተስማሙት በትናንትናው እለት ነው፡፡ እስራኤል ከዚህ በፊት ከዩኤኢና ባህሬን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኑነት ለመጀመር ስምምት ማድረጓ ይታወሳል፡፡ በተጨማሪም እስራኤል ከሱዳን ጋር ግንኙነት ለመጀመር ማሰቧ ይታወሳል፡፡