ሳዑዲ አረቢያ በ11 ሀገራት ላይ ጥላ የነበረውን የጉዞ እገዳ አነሳች
የጉዞ ክለከላው ቢነሳም ከሀገራቱ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚጓዙ ሰዎች በለይቶ ማቆያ መቆየት አለባቸው
ከ11 ሀገራት ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚጓዙ ሰዎች ከዛሬ ጀምሮ ያለምንም ክልከላ መግባት ይችላሉ ተብሏል
ሳዑዲ አረቢያ በ11 ሀገራት ላይ ጥላ የነበረውን የጉዞ እገዳ ማንሳቷን የሳዑዲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሳዑዲ አረቢያ የዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው በሀገራቱ ላይ የጉዞ እገዳው ተጥሎ የነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ታስቦ ነው።
የጉዞ ክልከላው ቢነሳም ከሀገራቱ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚጓዙ ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ መቆየት እንደሚጠበቅባቸውም ተነግሯል።
የዜና አግልግሎቱ የሳዑዲ አረቢያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፤ ዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ አየርላንድ፣ ጣሊያን ፖርቹጋል፣ ብሪታኒያ፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድ፣ ፈረንሳይ፣ እና ጃፓን ላይ ተጥሎ የነበረው የጉዞ ክልከላ ነው የተነሳው።
በዚህም መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ከ11 ሀገራት ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚጓዙ ሰዎች ያለምንም ክልከላ መግባት እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን መንገደኞቹ ሳውዲ ሲደርሱ በለይቶ ማቆያ እንደሚጠበቅባቸው ተነግሯል።
ሀገሪቱ የጉዞ ክልከላውን በ20 ሀገራት ላይ ጥላ የነበረ ሲሆን የጉዞ ክልከላው የተነሳላቸው ሀገራትም ከ20ዎቹ ውስጥ የነበሩ ናቸው ተብሏል።
የጉዞ ክልከላው በዘጠኝ ሀገራት ላይ እንደተጣለ የሚቆይ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፤ ክልከላው ከሚጸናባቸው ሀገራት ውስጥም ፓኪስታን፣ ብራዚል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱርክ፣ ግብጽ፣ ህንድ፣ ኢንዶንዢያ እና ጃፓን ይገኙበታል።