ኢትዮጵያውያንንን ጨምሮ በርካቶች ይቸገሩበት ነበር የተባለለት የሳዑዲ የ“ከፋላ” ስርዓት ተቀየረ
ስርዓቱ የተሻለ የስራ ሁኔታን ለመፍጠር ያልቻለ “አሳሪ” ህግ ነበር ተብሏል
ሪያድ ላለፉት 70 ዓመታት የተገበረችውን ይህን ስርዓት ከነገ ጀምሮ በአዲስ እንደምትተካ አስታውቃለች
ሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያንንን ጨምሮ የበርካታ ሃገራት ዜጎች ‘ይቸገሩበት ነበር’ የተባለለት የ“ከፋላ” ወይም የ‘ስፖንሰርሺፕ’ ስርዓት ቀየረች፡፡
ሪያድ ላለፉት 70 ዓመታት ተግብራው ነበር የተባለለት ስርዓቱ በአሰሪና ሰራተኞች መካከል መልካም ግንኙነትን ለመፍጠር ያላስቻለ እንደነበር ይነገራል፡፡
ሆኖም ስርዓቱ ከነገ እሁድ ጀምሮ በተሻሻለ አዲስ ህግ ተተክቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው የሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች የዘገቡት፡፡
አዲሱ ህግ ከአሁን ቀደም በአሰሪና ሰራተኞች መካከል እንዲኖር ይጠበቅ የነበረውን የ ‘ስፖንሰርሺፕ’ ስምምነት የሚያስቀር ነው፡፡
የ‘ስፖንሰርሺፕ’ ህጉ በአሳሪነቱ ነው ሳዑዲ በሚኖሩና በሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ጭምር የሚጠቀሰው፡፡
እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ፣ የተሻለ የስራ ዓይነትንና ቦታን ለመምረጥ የማያስችል እንደሆነም ይነገራል፡፡ የተቀጣሪዎች ፓስፖርት በቀጣሪዎች እጅ እንዲሆን፣ እንደፈለጋቸው እንዲያዙ እንዲያናዝዙ በሚፈቅደው በዚህ “አሳሪ” ህግ ምክንያት ብዙዎች ለስቃይና እንግልት ተዳርገዋልም ነው የሚባለው፡፡
የበርካታ ዓመታት የልፋት ውጤታቸውን ሳያገኙ ‘አመድ አፋሽ’ ሆነው የቀሩ ቀጣሪ ነን በሚሉ ደላሎች ገንዘባቸው የተነጠቁም ጥቂት አይደሉም፡፡
በእንዲህ ዐይነት መንገድ ለዐይነተ ብዙ ችግሮች የተዳረጉ ኢትዮጵያውያንን ሮሮ መስማትም የተለመደ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የውጭ ሃገራት የስራ ስምሪትን ለማሻሻል ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ ከተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ጋር እየሰራች መሆኗ ይታወሳል፡፡
ሳዑዲ የተሻለ የስራ እድልን እና የተሻለ የስራ ቦታን ለመፍጠር በማሰብ ህጉን ከነገ እሁድ ጀምሮ በአዲስ ለመተካት መዘጋጀቷም ተነግሯል፡፡
እርምጃው የስራ እንቅስቃሴን ለማቀላጠፍ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
እ.ኤ.አ እስከ 2019 መጨረሻ ድረስ በሳዑዲ የግል እና የመንግስት ሰራተኞች ቁጥር 8 ነጥብ 4 ሚሊዬን ገደማ እንደነበር የስታትስቲክስ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የውጭ ሃገራት ዜጎች ናቸው፡፡
የቀጣይ 5 ዓመታት የልማት ዕቅዶችን በቅርቡ ይፋ ያደረገችው ሳዑዲ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት 3 ትሪሊዬን ሪያል ኢንቨስት ለማድረግ መወጠኗን ማስታወቋ የሚታወስ ነው፡፡