ክትባቱ በሶስት ደረጃዎች ተከፍሎ እንደሚሰጥ የሳዑዲ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል
የመጀመሪያው ዙር ፋይዘር የተሰኘው የኮሮናቫይረስ ክትባት ሀገሯ የገባው ሳዑዲ በዛሬው ዕለት ክትባቱን ለዜጎቿ መስጠት ጀምራለች፡፡
ክትባቱ ለሀገሪቱ ዜጎች በሶስት ደረጃዎች ተከፍሎ እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን በመጀመሪያ ደረጃ እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ እና ለበሽታው ከፍተኛ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ይከተባሉ፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ ይከተባሉ የተባለ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ በሶስተኛ ደረጃ እንደሚከተቡ የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የጤና ሚኒስትሩ ታውፊቅ አል ራቢአህ እና የተወሰኑ ሰዎች ዛሬ ክትባቱን ወስደዋል፡፡ ሚኒስትሩ ክትባቱን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “ይህ የቀውሱ ፍጻሜ መጀመሪያ ነው” ብለዋል፡፡
ከ34 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ሳዑዲ ክትባቱን በነጻ ነው በመስጠት ላይ የምትገኘው፡፡ ሴሃቲ (Sehaty) በተሰኘ የኦንላይን መተግበሪያ ክትባቱን ለመውሰድ እስካሁን ከ100,000 በላይ ሰዎች መመዝገባቸውንም ገልፍ ቱዴይ ዘግቧል፡፡
ክትባቱ በሙከራ ደረጃ ላይ እያለ ውጤታማነቱ እና ጤናማነቱ መረጋገጡ ይታወቃል፡፡
በርካታ የበለጸጉ ሀገራት የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን ለማግኘት በመሯሯጥ ላይ ናቸው፡፡
የፋይዘር ክትባትን ቀድማ መጠቀም የጀመረችው ብሪታንያ ስትሆን ሌሎች ሀገራትም በመከተል ላይ ናቸው፡፡ አሜሪካ እና ካናዳም ክትባቱን መጠቀም የጀመሩ ሲሆን ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በ100 የስልጣን ቀናቸው 100 ሚሊዮን ዜጎች የክትባቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ማቀዳቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ከአውሮፓውያኑ ታህሣሥ 27 ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን መጠቀም እንደሚጀምሩ የህብረቱ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ ባዮኤንቴክ እና ፋይዘር የተሰኙ ክትባቶች በህብረቱ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ እውቅና የተሰጣቸው ክትባቶች መሆናቸውን ኮሚሽነሯ ኡርሱላ ቮን ደርሌይን ገልጸዋል፡፡