ሐጅ አድራጊዎች ከኮሮና ቫይረስ ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ 72 ሰዓት ያልሞላው የምስክር ወረቀት መያዝ አለባቸው
ሳዑዲ አረቢያ ለዘንድሮ የሐጅ ጉዞ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ማሟላት የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ሁኔታ ይፋ አደረገች።
የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሳዑዲ አረቢያ ጤና ቢሮን ዋቢ በማድረግ ባወጡት መረጃ በዘንድሮው ሐጅ ላይ ለመሳተፍ ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገሪቱ የሚገቡም ይሁን የሀገሪቱ ዜጎች በሀገሪቱ መንግስት እውቅና የተሰጣቸውን ክትባት የዙል ኸጃ ወር ከመግባቱ በፊት መውሰድ እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
‘አጅል’ የተባለ የሳዑዲ እልክትሮኒክ ጋዜጣም፣ በዘንድሮው ሐጅ ላይ ለመሳተፍ ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገሪቷ የሚገቡ የሐጅ አድራጊዎች በዓለም ጤና ድርጅት እውቅና የተሰጠውን የኮሮና ቫይረስ ክትባት መውሰድ እንደሚጠበቅባቸው አስነብቧል።
ክትባቱንም የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መጠን (ዶዝ) መውሰድ አለባቸው የተባለ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዙር ክትባቱንም ወደ ሳዑዲ ከመግባቸው አንድ ሳምንት በፊት መከተብ እንዳለባቸውም ተነግሯል።
በስፍራው የሚሰሩ ሰዎች በሙሉ ሁለቱን ዶዝ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን የሐጅ ስነ ስርዓቱ ከመጀመሩ በፊት መውሰድ እንደሚጠበቅባቸው በመመሪያው ተቀምጧል።
ከዚህ በተጨማሪም የዘንድሮ ሐጅ አድራጊዎች ከኮሮና ቫይረስ ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ 72 ሰዓት ያልሞላው የምስክር ወረቀት መያዝ እንደሚጠበቅባቸውም ተነግሯል።
እንዲሁም ሐጅ አድራጊዎቹ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ከገቡ በኋላ ለ72 ሰዓታት ኳራንቲን ውስጥ መቆየት እንደሚጠበቅባቸውም መገናኛ ብዙሃ ዘግበዋል።