ሳዑዲ አረቢያ በየዕለቱ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ እያገኘች መሆኗን ገለጸች
ሀገሪቱ ገቢውን እያገኘች ያለው ከነዳጅ ንግድ ሲሆን፤ ዕለታዊ የነዳጅ የማምረት አቅሟ ከ10 ሚሊየን በላይ በርሜል ደርሷል
ሳዑዲ አረቢያ በየወሩ 30 ቢሊየን ዶላር ገቢ እያገኘች መሆኗን አስታውቃለች
የመካከለኛው ምስራቅ ሀገር ሳዑዲ አረቢያ በየዕለቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር እያገኘች እንደሆነ ገልጻለች።
ከዓለማችን ነዳጅ አምራች እና ሻጭ ሀገሮች መካከል ዋነኛዋ የሆነችው ሳውዲ አረቢያ እለታዊ ነዳጅ የማምረት አቅሟ ከ10 ሚሊየን በላይ በርሜል እንደደረሰ የሀገሪቱ ፋይናንስ ሚኒስትር አስታውቋል።
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት መካከል የነዳጅ ዋጋው በየዕለቱ በመጨመር ላይ ሲሆን፤ አንድ በርሜል ነዳጅ 112 ዶላር በመሸጥ ላይ ይገኛል።
ይህ መሆኑ ደግሞ ሳውዲ አረቢያ ከነዳጅ የምታገኘው ገቢም በዚያው ልክ በመጨመር ላይ እንደሆነም ተገልጿል።
ሀገሪቱ አሁን እያገኘች ያለው ገቢ ባሳለፍነው ጥር እና መጋቢት ላይ ከተገኘው ጋር ሲነጻጸር የ15 ቢሊየን ዶላር ብልጫ እንዳለውም የሳዑዲ መንግስታዊ ሚዲያ አል አረቢያ ዘግቧል።
ቻይና፣ ህንድ፣ ጃፓን ፣ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ደግሞ የሳዑዲ አረቢያን ነዳጅ በገፍ የሚገዙ ሀገራት እንደሆኑ ዘገባው አክሏል።
ሀገሪቱ በመጋቢት ወር ላይ ብቻ 37 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ከነዳጅ ገቢ ያገኘች ሲሆን በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በሚፈጠረው የነዳጅ ገበያ ዋጋ መጨመር በቀጣይ ወራት ሊገኝ የሚችለው የነዳጅ ገቢ እንደሚያድግ ይጠበቃል።