ሳዑዲ በግብጽ ማዕከላዊ ባንክ 5 ቢሊዮን ዶላር አስቀመጠች
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ግብጽ ከፍተኛ ምጣኔ ሃብታዊ ችግር ላይ መውደቋ ተነግሯል
ገንዘቡ በዩክሬን ጦርነት የተጎዳውን የግብጽን ምጣኔ ሃብት ለመደጎም የሚውል ነው ተብሏል
ሳዑዲ አረቢያ የጠለቀ ታሪካዊ ግንኙነት ያላት እህት ሃገር ባለቻት ግብጽ ማዕከላዊ ባንክ 5 ቢሊዮን ዶላር አስቀመጠች፡፡
ገንዘቡ በንጉስ ሳልማን እና በልጃቸው በልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን ትዕዛር በግብጽ ማዕከላዊ ባንክ እንዲቀመጥ የተደረገ ነው፡፡
ሪያድ ድጋፉን ያደረገችው በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ግብጽ ከፍተኛ ምጣኔ ሃብታዊ ችግር ላይ መውደቋን ተከትሎ ነው፡፡
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በያዝነው ወር መባቻ በሪያድ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ካይሮ ችግሩን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ. ኤም. ኤፍ) የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግላት ከሳምንት በፊት ጠይቃ ነበር፡፡
ሆኖም የጠበቀ ግንኙነታቸውን ያስታወሰችው ሳዑዲ የ5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን አስታውቃለች፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ የግብጽ ፓውንድ የመግዛት አቅም ተዳክሟል፡፡ ከአሜሪካ ዶላር ያለው የምንዛሬ ደረጃም አሽቆልቁሏል፡፡ ከባለፈው ህዳር ወር ወዲህ ብቻ በፊት ከነበረበት የ15 በመቶ ማሽቆልቆል አሳይቷል፡፡ አንድ የአሜሪካ ዶላርም በ18 ነጥብ 24 ፓውንድ ነበር ሲመነዘር የነበረው፡፡
ይህን ተከትሎም የግብጽ ማዕከላዊ ባንክ ችግሩን ለመሻገር የሚያስችሉ የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎችን ሲወስድ ነበረ፡፡ የወለድ ምጣኔንም ከፍ አድርጓል፡፡ ችግሩን ለማለዘብ የሚያስችል የ7 ነጥብ 05 ቢሊዮን ዶላር አስቸኳይ የእርዳታ መርሃ ግብርንም ይፋ አድርጓል ባሳለፍነው ሳምንት፡፡
ከ102 ሚሊዮን እንደሚልቅ ከሚገመተው የግብፅ ህዝብ ውስጥ 30 በመቶው ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ነው። ስንዴን ከውጭ ከሚያስገቡ ቀዳሚ የዓለማችን ሃገራት መካከልም ግብጽ ቀዳሚዋ ነች፡፡ ከሩሲያ እና ዩክሬን ይገባ የነበረው ስንዴ በመቋረጡ ከህንድ ለማስገባት መስማማቷም ይታወሳል፡፡
ባሳለፍነው ጥቅምት ለግብጽ 3 ቢሊዮን ዶላር የሰጠችው ሳዑዲ ቀደም ሲል በግብጽ ማዕከላዊ ባንክ አስቀምጣ የነበረውን የ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የመክፈያ ጊዜ አራዝማለች፡፡ ይህም ሪያድ የአሁኑን ጨምሮ በግብጽ ማዕከላዊ ባንክ ያስቀመጠችው አጠቃላይ ዶላር መጠን 10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የሚያሳይ ነው፡፡
ግብጽ ትናንት ማክሰኞ ከኳታር ጋር የ5 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ስምምነት ማድረጓ የሚታወስ ነው፡፡