አማጽያኑ ጅዳ የሚገኘውን የሳዑዲ ግዙፍ የነዳጅ ማከማቻ ስፍራ አጥቅተዋል
ጅዳ ከተማ የሚገኘውን ግዙፉን የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማከማቻ ጣቢያ ያጠቁትና በየመን የሚንቀሳቀሱት የሃውሲ አማጽያን ዓለም አቀፋዊ ውግዘትን እያስተናገዱ ነው፡፡
በሳዑዲ የሚመራው የአረብ ሃገራት ጥምር ጦር አማጽያኑን አስጠንቅቋል፡፡ ጥቃቱ ለ16ኛ ጊዜ የተፈጸመ መሆኑን በማስታወስም “አትፈታተኑኝ” ሲል አሳስቧል፡፡
የሳዑዲ ጦር አማጽያኑ በደቡባዊ እና ደቡብ ምዕራባዊ የሃገሪቱ አካባቢዎች የፈጸሟቸውን 12 የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እና የሚሳዔል ጥቃት ማክሸፉን ያስታወቁት የጥምር ጦሩ ቃል አቀባይ ብ/ጄ ቱርኪ አል ማሊኪ በዓለም የነዳጅ አቅርቦት ላይ እክልን ለመፍጠር በማሰብ የጅዳው ጥቃት መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡
ከጥቃቶቹ መካል አንዱ ነው ጅዳ የሚገኘውን የአራምኮ የነዳጅ ማከማቻ ዴፖ የመታው፡፡ ጀዛን የሚገኘው የአል ሙክታራ ዴፖ መመታንም የሳዑዲ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
አሜሪካ የኢራን የረዘመ እጅ በጥቃቱ አለበት በሚል ኢራንን ተችታለች፡፡
ለአማጽያኑ መሳሪያዎችን በማቅረብ ድጋፍ በማድረግ ሁኔታዎችን ማመቻቸቷንም የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ተናግረዋል፡፡
ሱሊቫን የአሁኑን ጨምሮ የሰቪል ማህበረሰብ መገልገያ መሰረተ ልማቶችን ዒላማ አድርገው ከአሁን ቀደም የተፈጸሙት ጥቃቶች በግልጽ በኢራን ድጋፍ የተፈጸሙ ናቸው ሲሉም ኮንነዋል፤ የኢራን ድርጊት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአማጽያኑ ላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የሚጥስ መሆኑን በመጠቆም፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም ሃገራቸው የሳዑዲን ጥቃችን የመከላከል አቅም ለማሳደግ እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡
አረብ ኤሚሬትም የሳዑዲ ደህንነት ጉዳይ የራሷ መሆኑን በማሳሰብ ጥቃቱን አውግዛለች፡፡
በሳዑዲ ሁለተኛዋ ግዙፍ ከተማ ጅዳ የሚገኘው የነዳጅ ማከማቻ ከሳዑዲ አጠቃላይ የነዳጅ አቅርቦት ሩብ ያህሉን የሚሸፍን ነው፡፡ የቤንዚን፣ የናፍጣ እና የአውሮፕላን ነዳጅን አከማችቶም ይዟል፡፡
ትናትንት አርብ በአማጽያኑ የተፈጸመው ጥቃትም ይህን ግዙፍ የነዳጅ ማከማቻ ዒላማ ያደረገ ነው፡፡ በጥቃቱም ከማከማቻው የነዳጅ ታንከሮች ሁለቱ በእሳት መያያዛቸው ተነግሯል፡፡ ሆኖም እሳቱ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ የደረሰ ምንም ዐይነት ሰብዓዊ ጉዳት የለም፡፡
ሳዑዲ ነገ እሁድ የፎርሙላ 1 የመኪና ውድድር የምታስተናግድ ይሆናል፡፡