ሳኡዲ አረቢያ ለእስያ ገዥዎች የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ልትቀንስ ነው
አሁን የዓለም የነዳጅ ገበያ ላይ ባለው ከመጠን በላይ አቅርቦት መጥለቅለቁ መረጃዎች ይጠቁማሉ
ሪያድ የዋጋ ቅነሳ የምታደርገው ሩሲያ የነዳጅ ምርቷን ወደ እስያ ገበያ መላክ መጀመሯ ተከትሎ ነው ተብሏል
ከፍተኛ የነዳጅ ላኪ ሳኡዲ አረቢያ ለእስያ ገዥዎች በ15 ወራት ውስጥ የድፍድፍ ነዳጅ የዋጋ ቅነሳ ልታደርግ እንደምትችል ተገለጸ፡፡
ሳዑዲ የዋጋ ቅነሳ የምታዳርገው የዓለም የነዳጅ ገበያ ላይ ባለው ከመጠን በላይ አቅርቦት ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
በተለይም ነዳጇን በአውሮፓ ምድር እንዳትሸጥ እገዳ የተጣለባት ሩሲያ የነዳጅ ምርቷን ወደ እስያ ገበያ መላክ መጀመሯ ሳዑዲ አረቢያ በነዳጅ ዋጋ ላይ ቅነሳ እንድታደርግ አስገዳጅ ሁኔታ እንደፈጠረባት ይነገራል፡፡
በዚህም መሰረት ግዙፉ የነዳጅ ኩባንያ ሳዑዲ አራምኮ በዱባይ ቤንችማርክ ከተወሰደው እርምጃ ጋር በተያያዘ በየካቲት ወር የመሸጫ ዋጋውን በበርሚል በ1 ነጥብ 50 ዶላር ሊቀንስ ይችላል እንደሚችል ተመላክቷል።
የዋጋ ማስተካከያው በህዳር 2021 መጨረሻ ወደ ነበረው ዋጋ የሚመልስና ከዱባይ ቤንች ማርክ አንጻር የ1 ነጥብ 75 ዶላር ብልጫ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው፡፡
ሳዑዲ አራምኮ የድፍድፍ ነዳጅ የዋጋ ተመን የሚያወጣው ከደንበኞች በሚሰጡ ምክሮች እና በዘይት ዋጋ ላይ ባለፈው ወር ላይ የተደረገውን ለውጥ በማስላት በምርቶች ዋጋ ላይ በመመስረት ነው፡፡
ሮይተርስ ያናገራቸው አንድ አንድ ምላሽ ሰጪ "የቅርብ ጊዜ የገበያ ሁኔታ ደብዝዟል፤ ብዙ የሩሲያ የነዳጅ በርሜሎች ወደ እስያ ይጎርፋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ፍላጎት እየጨመረ አይደለም" ብለዋል፡፡
ለቻይና እና ህንድ ቀዳሚ ድፍድፍ አቅራቢ መሆን የቻለችው ሩሲያ ፤ አሁን ላይ የእስያው ገበያ ለመቆጣጠር እየታተረች እንደሆነም እየተገረ ነው፡፡
ምንም እንኳን ሞስኮ ባለፈው ሳምንት በሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ ላይ የዋጋ ጣሪያን ለሚመለከቱ ሀገራት የድፍድፍ ነዳጅ ሽያጭ ብታግድም ፤ በእስያ የሚገኙ ቁልፍ የነዳጅ ደንበኞቿ የዋጋ ማሻሻያ ጥምረትን ባለመቀላቀላቸው ነዳጅን ካለምንም ችግር በማቅረብ ላይ ናት፡፡
ከሩሲያ -ዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ከምዕራበውያን ጋር የነበራት የንግድ ልውውጥ ሙሉ በሙሉ ያቋረጠችው ሞስኮ፤ የተጣሉባት ማዕቀቦች የማይነሱ ከሆነ ወደ አውሮፓ ነዳጅ እንደማትልክ መግለጿ አይዘነጋም፡፡