ሞሪንሆ በሳኡዲ የአለማችን ውድ አሰልጣኝ የሚያደርግ ኮንትራት ቀርቦላቸዋል
ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ የሳኡዲ አረቢያ ብሄራዊ ቡድንን ለማሰልጠን ከተስማሙ 125 ሚሊየን ዶላር ይከፈላቸዋል ነው የተባለው
ጆዜ ሞሪንሆ ከሮማ ጋር ያላቸው ውል በ2024 ይጠናቀቃል
ፖርቹጋላዊው የሮማ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ የሳኡዲ አረቢያ ብሄራዊ ቡድንን እንዲያሰለጥኑ አጓጊ ደመወዝ ቀርቦላቸዋል።
ሞሪንሆ በጣሊያኑ ክለብ የሚያቆያቸው ኮንትራት በ2024 ይጠናቀቃል።
ራሳቸውን “ልዩ ሰው ነኝ” ብለው የሚጠሩት አወዛጋቢው አሰልጣኝ ከሳኡዲ የቀረበላቸው የ100 ሚሊየን ፓውንድ ደመወዝ ግን ውላቸውን ሳያጠናቅቁ ጭልፊቶቹን ማሰልጠን እንዲጀምሩ ሊያደርጋቸው እንደሚችል የጣሊያኑ ተነባቢ ጋዜጣ ኮሬር ዴሎ ስፖርት አስነብቧል።
ሞሪንሆ የሳኡዲ ብሄራዊ ቡድንን ለማሰልጠን በአመት 60 ሚሊየን ዩሮ ይከፈላቸዋል ያለው ጋዜጣው፥ የሁለት አመት ውሉ የ60 አመቱን ፖርቹጋላዊ የአለማችን ውዱ አሰልጣኝ እንደሚያደርጋቸው ዘግቧል።
ሮማ እስካሁን የሞሪንሆን ውል ለማደስ ግልጽ ፍላጎቱን አላሳየም የሚለው ጎል ዶት ኮም በበኩሉ፥ አሰልጣኙ በሮማ ለመቆየት ክለቡ ተጫዋቾችን ማስፈርም እንደሚኖርበት ማሳሰባቸውን አስታውሷል።
ጆዜ ሞሪንሆ ከፈርናንዶ ሳንቶስ ስንብት በኋላ የፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድንን እንደሚያሰለጥኑ ቢጠበቅም ከሮማ ጋር መቆየትን መምረጣቸው አይዘነጋም።
በቅርቡም ቼልሲን ዳግም እንደሚይዙ በስፋት ቢነገርም በጣሊያኑ ክለብ ጋር ለመቆየት መወሰናቸውን የሚያነሱ የስፖርት ተንታኞች ወደ ሳኡዲ የማምራታቸውን ጉዳይ አነስተኛ እድል ይሰጡታል።
ሶስት ጊዜ የእስያ ዋንጫ ሻምፒዮን የሆነው የሳኡዲ አረቢያ ብሄራዊ ቡድን፥ በአለም ዋንጫ ስድስት ጊዜ ተሳትፏል።
በኳታር በተዘጋጀው የአለም ዋንጫ ሻምፒዮን የሆነችውን አርጀንቲናን በማሸነፍም የማይረሳ ታሪክ ማጻፍ መቻሉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።