ሳዑዲ አረቢያ እና ኳታር የሻከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማለስለስ ተስማምተዋል
የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፈይሰል ቢን ፈርሃን ወደ ኳታር ማቅናታቸውን የሃገሪቱ የዜና አገልግሎት ዘገበ፡፡
ሚኒስትሩ ዶሃ ደርሰው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሃመድ ቢን አብዱራህማን ቢን ጃሲም አል ታኒ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
በአቀባበሉ ጊዜ ከአባታቸው ከንጉስ ሳልማን እንዲሁም ከወንድማቸው ከልዑል አልጋወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን የተላከ የሰላምታ መልዕክትን ማድረሳቸውን ዘገባው ያተተው፡፡
በዶሃ ከኳታሩ ኢምር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ እንዲሁም ከሼክ መሃመድ ቢን አብዱራህማን ቢን ጃሲም አል ታኒ ጋር መምከራቸውንም ጠቁሟል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ እና ኳታር እ.ኤ.አ ከ2017 ወዲህ የሻከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ነው ያላቸው፡፡ ሆኖም የሻከረውን ግንኙነት ዳግም ለማለስለስ ባሳለፍነው ጥር መዲና ተብሎ በሚጠራው የሳዑዲ አካባቢ በምትገኘው አል ዑላ ከተማ በተካሄደው የባህረ ሰላጤው ሃገራት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተስማምተዋል፡፡
የኳታሩ ኢምር በተገኙበት በተካሄደው ጉባዔ የተፈረመው የአል ዑላ ስምምነት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን ጨምሮ ከኳታር ጋር የነበራቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጠው የነበሩ ሌሎችንም የገልፍ ሃገራት ያካትታል፡፡