የባሕረ ሰላጤው ሀገራትና ግብፅ ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኑነት ወደ ነበረበት ለመመለስ መወሰናቸው ተገለጸ
ሳዑዲ ፣ ዩኤኢ ፣ ባህሬን እና ግብፅ ከ 3 ዓመታት በላይ በኳታር ላይ ማዕቀብ ጥለው ቆይተዋል
ሀገራቱ ውሳኔውን ያሳወቁት 41ኛውን የባሕረ ሰላጤው ትብብር ም/ቤት ጉባዔ ተከትሎ ነው
ሳዑዲ አረቢያ ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፣ ባህሬን እና ግብፅ ለሦስት ዓመት ተኩል በየብስ ፣ በባሕርና በአየር እንዳትገናኛቸው ማዕቀብ ጥለውባት ከነበሩት ኳታር ጋር ዳግም የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጀመራቸውን የሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ፡፡
ሀገራቱ ከኳታር ጋር የነበራቸው ውዝግብ መፈታቱንና ሙሉ ለሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው መመለሱን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ ለሦስት ዓመት ተኩል በዶሃና በሪያድ መካከል የነበረው ውዝግብ ማብቃቱና የዲፕሎማሲያዊ ግንኑነቱ ተግባራዊነት በቅርቡ እንደሚጀመርም ተገልጿል፡፡
የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳዑዲ አረቢያ ከኳታር ጋር ያላትን ግንኙነት ወደነበረበት እንደምትመልስ ትናንት ማክሰኞ ዕለት ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ልዑል ፈይሰል ቢን ፋርሃን አል ሳዑድ ከ 41 ኛው የባህረ ሰላጤ የትብብር ምክር ቤት ስብሰባ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሪያድ የአል ኡላ መግለጫን ከፈረመች በኋላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን እንደምትጀምር ነው የገለጹት፡፡
ልዑል ፈይሰል በሳዑዲ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በምትገኘው በረሃማዋ የአል ኡላ ከተማ በሰጡት መግለጫ የትናንትናውን ዕለት “የልዩነት ነጥቦች ተፈተው አንድነትና ሰላም ዕውን የሆነበት ዕለት ነው” ማለታቸውን ዘናሽናል ዘገቧል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፣ ባህሬን እና ግብፅ ከኳታር ጋር ተቋርጦ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ሙሉ ለሙሉ ወደ ነበረበት እዲመለስ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዳላቸውም የሳዑዲው ዉጭ ጉዳይ ሚነስትር አስታውቀዋል፡፡
የዩኤኢ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ዶ/ር አንዋር ጋርጋሽ ለአል አረቢያ በሰጡት አስተያየት ጉባዔው “የግጭት እና የረዥም ጊዜ አለመግባባት ታሪክ የቀየረ ነው” ብለዋል፡፡
በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት አሁን የተደረሰው ስምምነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም የሚታመን ሲሆን ይህንን ለማድረግ ብዙ ሥራዎች መሰራታቸውን ሳዑዲ አረቢያ ገልጻለች፡፡ የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን፣ የኳታሩ አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል-ታኒ ትናንት ለባሕረ ሰላጤው ትብብር ምክር ቤት አል ኡላ ከተማ ሲደርሱ እንደተቀበሏቸው ይታወሳል፡፡