ዩኤኢ ከኳታር ጋር ያላትን የየብስ የባሕር እና የአየር ክልል ድንበር ዛሬ ትከፍታለች
የኳታር አየር መንገድ ሀሙስ ዕለት ወደ ሳዑዲ አረቢያ በረራ ጀምሯል
በቅርቡ ኤምባሲ ለመክፈት እና ሁሉንም ግንኙነቶች ለማደስ ተግባራዊ እርምጃዎች ይጀመራሉ ተብሏል
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከኳታር ጋር የምትዋሰንባቸው የአየር ፣ የየብስ እና የባህር ድንበሮች ዛሬ እንደሚከፈቱ አስታውቃለች፡፡
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ጸሐፊ ካሊድ አብዱላህ ቤልሀውል ከኳታር ጋር የሁለትዮሽ ንግግር እደሚጀመር ለኤሚሬትስ ዜና አገልግሎት አስታውቀዋል፡፡ በቋታር ላይ ተጥለው የነበሩ እገዳዎች እንዲያበቁ ተግባራዊ ስራ መጀመሩን የገለጹት ጸኃፊው ፣ ውሳኔው የተወሰነው ከሰሞኑ ከተካሄደው የገልፍ ሀገራት ጉባዔ በኋላ ነው ብለዋል፡፡
ከኳታር ጋር ያለው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የየብስ ፣ የባሕርና የአየር ክልል ድንበር ክፍት እንደሚሆንና ለሚመለከታቸው የዩኤኢ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እንደተነገራቸው ተገልጿል፡፡ ድንበሮቹ ከዛሬ ጀምረው ክፍት እንደሚሆኑ የገለጹት ምክትል ጸሐፊው ዩኤኢም ለዚህ ስራ ቁርጠኛ እንደሆነች ተናግረዋል፡፡ ዩኤኢ የወሰደችው እርምጃ የገልፍ ሀገራትን ትብብርና አንድነት እንደሚያጠናክርም ነው የገለጹት፡፡
ይህ ውሳኔ ይፋ የተደረገው ሳዑዲ አረቢያና ኳታር የቀደመ ግንኙነታቸውን ለመመለስ ከተስመሙ እና ሳዑዲ ሁሉንም ድንበሮቿን እንደምትከፍት ካስታወቀች በኋላ ነው፡፡
የዩኤኢ ጠቅላላ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን በኳታርና በዩኤኢ መካከል በዕቅድ የተያዙም ሆነ ያልታቀዱ በረራዎች ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረጉ አስታውቋል፡፡ የኤቲሃድ አየር መንገድ ቃል አቀባይ በረራው እንዲጀመር መወሰኑ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ የአየር ክልሉ ድጋሚ መከፈቱ በአቡዳቢና በዶሃ መካከል ያለው የቱሪዝምና የንግድ ግንኙነት እንዲጠናከር ያደርጋል ሲሉም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡ ኤቲሃድ በዚህ ዙሪያ የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎችን በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ የኳታር አየር መንገድ ሀሙስ ዕለት ወደ ሳዑዲ አረቢያ በረራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
የዩኤኢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አንዋር ጋርጋሽ ከኳታር ጋር የትራንስፖርት አገልግሎትን ለመጀመርና የንግድ ትስስሩን ለመመለስ ተግባራዊ እርምጃዎች እንደሚጀመሩ አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት ኤምባሲዎችንና ቆንስላዎችን መክፈትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች በፍጥነት ይከናወናሉ ብለዋል፡፡ በሳዑዲ አረቢያ አል ኡላ የተደረሰው ስምምነት ስትራቴጂያዊ ነው ሲሉ የተናገሩት ዶ/ር ጋርጋሽ ፣ ዩኤኢ በሳዑዲ ከተደረሰው ስምምነት ጀርባ እንደነበረችም ተናግረዋል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች፣ ባህሬንና ግብፅ ለሦስት ዓመት ተኩል ከኳታር ጋር ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ግንኙነታቸውን ለማደስ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡