በፍልስጤም የሳኡዲ አምባሳደር የሚመሩት ልዕክ ዌስትባንክ ገባ
የሳኡዲ ልኡክ ከ1993ቱ የኦስሎ ስምምነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ወደ ዌስትባንክ የገባው
ሳኡዲ የፍልስጤም ጉዳይ ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ለመድረስ ወሳኝ ነጥብ መሆኑን ማሳወቋ ይታወሳል
በፍልስጤም የሳኡዲ አረቢያ የመጀመሪያው አምባሳደር የመሩት ልኡክ በዛሬው እለት ዌስትባንክ ገብቷል።
አምባሳደር ናይፍ አል ሱዳይሪ ከዮርዳኖስ በአል ካርማ መተላለፊያ በኩል ወደ ዌስትባንክ መግባታቸውን አናዶሉ ዘግቧል።
አምባሳደር ሱዳይሪ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሀሙድ አባስ የሚያቀርቡ ሲሆን፥ ከፕሬዝዳንቱ እና ሌሎች ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ ተገልጿል።
አምባሳደሩ እና የሚመሩት ልኡክ በራማላህ ጉብኝት እንደሚያደርግም ነው የተዘገበው።
በ1993 በኦስሎ ከተፈረመውና የእስራኤልና ፍልስጤምን ግጭት ያስቆማል ከተባለው ስምምነት በኋላ ሳኡዲ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለስልጣናቷ ዌስትባንክ ገብተዋል።
በዮርዳኖስ የሳኡዲ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ሱዳይሪ ባለፈው ነሃሴ ወር የፍልስጤም አምባሳደርነትንም ደርበው እንዲይዙ መሾማቸው የሚታወስ ነው።
ሳኡዲ በእስራኤል ቆንስላዋን መክፈት አትችልም ያለው የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፥ “አምባሳደር ሱዳይሪ የፍልስጤም ተወካዮችን በእየሩሳሌም ማግኘት ይችላሉ፤ ነገር ግን ቋሚ መቀመጫ አይኖራቸውም” ሲል ለሪያድ ማሳሰቢያ መላኩ አይዘነጋም።
ሳኡዲ አምባሳደሯን ወደ ዌስትባንክ የላከችው ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ለመፈራረም ንግግራችን ቀጥሏል ባለች ማግስት ነው።
የሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን በቅርቡ ከአሜሪካው ፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ የፍልስጤማውያን ጥያቄ ምላሽ ካላገኘ ከእስራኤል ጋር የጀመርነው ንግግር ፍሬያማ አይሆንም ሲሉ ተደምጠዋል።
በአሜሪካ አደራዳሪነት እየተካሄደ ያለው የሰላም ንግግር እስራኤል በዌስትባንክ በቀጠለችው የሰፈራ ፕሮግራም ምክንያት እንዳይሰናከል ስጋት ተፈጥሯል።
ሳኡዲ አምባሳደሯን በዌስትባንክ እና ራማላህ ለጉብኝት መላኳም መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ለመመልከት ያለመ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።